ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ ካይሮ ሲደርሱ የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱለፋታህ አልሲሲ አቀባበል አድርገውላቸዋል
የአቡዳቢ ልዑል አልጋ ወራሽና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ አዛዥ ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አልናህያን ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ካይሮ ገብተዋል፡፡
ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ ካይሮ ሲደርሱ የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱለፋታህ አልሲሲ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
ልዑል አልጋ ወራሹ ከፕሬዚዳንት አልሲሲ ጋር በሁለቱ ሀገራት ግንኙነትና ትብብር ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል፡፡ በሁለቱ ሀገራት በጋራ በሚሰሩ ሥራዎች፣ በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውንም ነው ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ በትዊተር ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት፡፡ ከግብፁ ፕሬዚዳንት ጋር ተገናኝተው በመነጋገራቸውም ደስተኛ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡
ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው የሁለቱ ሀገራት መሪዎች እ.ኤ.አ ከ2014 ጀምሮ አንዳቸው በሌላኛቸው በድምሩ 22 ጉብኝቶችን አድርገዋል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ከኢትዮጵያም ጋር የቆየ ወዳጅነት ያላት ሲሆን በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያን መምራት ከጀመሩ ወዲህ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ ተጠናክሯል፡፡ ባለፉት የሁለት ዓመት ከግማሽ ጊዜያት ዩኤኢ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የገንዘብ እና የኮሮናቫይረስ ህክምና ቁሳቁሶችን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጓ ይታወቃል፡፡
በቅርቡም ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ በማህበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸው “ወንድሜ” ያሏቸውን ጠ/ሚ ዐቢይን “ለሕዝቡ እና ለሀገሩ ለውጥ የሚታትር…” በሚል አድናቆታቸውን መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡