ሲዳማ ራሱን ችሎ በክልልነት ይደራጃል ወይስ ሊፈርስ ከሚደገስለት የደቡብ ክልል ሌሎች ብሄሮች ጋር ይጣመራል?
ሲዳማ ራሱን ችሎ በክልልነት ይደራጃል ወይስ ሊፈርስ ከሚደገስለት የደቡብ ክልል ሌሎች ብሄሮች ጋር ይጣመራል?
ለዘመናት የቆየው የሲዳማ በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ አሁን በምንገኝበት ዓመት ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም ረቡዕ ዕለት በተደረገው ሕዝበ ውሳኔ በህዝቡ ይሁኝታ ቢያገኝም እስካሁን ተግባራዊ አልሆነም፡፡ ህዝበ ዉሳኔው ከተካሄደ 7ኛ ወሩ ላይ ይገኛል፡፡
በሕገመንግስቱ አንቀጽ 47 በተጠቀሰው መሰረት ፣ አዲስ ክልል ሲቋቋም መሟላት ካለባቸው ሂደቶች መካከል የሲዳማን ምሉዕ ክልልነት ለማረጋገጥ የሚቀረው የደቡብ ክልል ለአዲሱ የሲዳማ ክልል ስልጣን ማስረከብ ብቻ ነው፡፡ ይሄን ሂደት ካለፈ በሕዝበ ውሳኔ የሚፈጠረው አዲስ ክልል ጥያቄ ማቅረብ ሳያስፈልገው በቀጥታ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፓብሊክ አባል ሲሆን እንደሚችል አንቀጽ 47 በንዑስ አንቀጽ 3/ሠ ይደነግጋል፡፡
በርግጥ በዚህ ሂደት ክልል መመስረት በኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ መሆኑ የሲዳማ ክልልነት በፍጥነት ተግባራዊ እንዳይሆን ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ ነው፡፡ ያም ሆኖ ባለፉት 6 ወራት የሽግግር ተግባራት ሲከናወኑ እንደነበር የሲዳማ ባለስልጣናት በተለያዩ ጊዜያት ተናግረዋል፡፡
የነባሩ ክልል (የደቡብ) አመራሮችና አዲስ የሚመሰረተው ክልል (የሲዳማ) ተወካዮች የተካተቱበት የጋራ ጥምር ኮሚቴ ተቋቁሞ እስካሁን በጋራ ያፈሯቸውን ንብረቶች የመለየት፣ ለጋራ ንብረቶች ዋጋ የማውጣት ፣ ክፍፍል የማድረግና ሌሎችንም ተያያዥ ሂደቶችን ማከናወናቸው ተገልጿል፡፡ ህዝበ ዉሳኔውን ተከትሎ በጋራ የፈሩ ንብረቶች ዋጋ በገንዘብ ተሰልቶ ክፍፍል እንዲደረግ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ከዚህ ቀደም መወሰኑ ይታወቃል፡፡ የሀዋሳ ከተማ ጉዳይን በተመለከተም ነባሩ የደቡብ ክልል ለሁለት የምርጫ ዘመን (ለ10 ዓመታት) ከተማዋን በዋና ከተማነት ከሲዳማ ጋር በደባልነት የሚጠቀም ሲሆን የከተማዋ ተጠሪነት የሲዳማ ክልል ይሆናል፡፡
ከአል ዐይን ዜና ጋር በስልክ ቆይታ ያደረጉት የሲዳማ ዞን የህዝብ ግንኙነት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገነነ አበራ በዞኑ ደረጃ ለክልልነት የሚያስፈልጉ ቅድመ ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡ አዲስ የሚመሰረተው ክልል መዋቅር እና መሰል ጉዳዮችም መጠናቀቃቸውን ነው አቶ ገነነ የገለጹት፡፡ የክልሉ የቀጣይ 10 ዓመታት ዕቅድ እና ሕገ መንግስትም ተዘጋጅቶ ህብረተሰቡ ዉይይት እንዳደረገባቸውም አብራርተዋል፡፡
በመሆኑም እንደ አቶ ገነነ አበራ ገለጻ ሲዳማ ክልላዊ መዋቅሩን ተግባራዊ ለማድረግ ከደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ስልጣን በይፋ መረከብ ብቻ ነው የሚቀረው፡፡
በሲዳማ በኩል በአጭር ጊዜ ውስጥ ስልጣን እንዲያስረክብ ለነባሩ የደቡብ ክልል ጥያቄ መቅረቡን ያነሱት አቶ ገነነ ክልሉ ዉስጥ ባሉ የተለያዩ ችግሮች የተነሳ የተወሰነ ጊዜ እንዲሰጠው ክልሉ መጠየቁን ተናግረዋል፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ የደቡብ ክልል የሲዳማ ክልልነት መሬት ላይ የሚወርድበትን ስልጣን እንደሚያስረክብ እና አዲሱ ክልል ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በይፋ ሊመሰረት እንደሚችል አቶ ገነነ ለአል ዐይን ይፋ አድርገዋል፡፡ አሁን ካለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አንጻር የተቆረጠ ቀን ባይቀመጥም በሲዳማ በኩል ፣ከደቡብ ክልል ጋር ያሉ ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ፣ በቀጣዩ ሀምሌ ወር ክልሉን በይፋ ለመመስረት መታቀዱንም ነው አቶ ገነነ በቆይታችን የተናገሩት፡፡
የደቡብ ክልልን በመበተን በአዲስ መልክ በተለያዩ ክልሎች ለማደራጀት በተጀመረው ስራ ፣ ሲዳማን በአቅራቢያው ከሚገኙ ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ፣ ማለትም ከጌዲኦ ዞን ፣ ከአማሮ አና ከቡርጂ ወረዳዎች ጋር በአንድ ክልል ለማደራጀት ታቅዷል በሚል በማህበራዊ ሚዲያዎች ስለሚሰራጩ መረጃዎችም ጥያቄ አንስተንላቸው አቶ ገነነ የሀሰት መረጃዎች ስለመሆናቸው ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡
አቶ ገነነ ይሄን ጥያቄ ሲመልሱ “የሲዳማ ጉዳይ ያለቀለት ነው” ብለዋል፡፡ በቀድሞው የደቡብ ክልል ገዢ ፓርቲ ደኢህዴን በተዋቀረው አጥኚ ቡድንም ይሁን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በተዋቀረው 80 አባላት ያሉት ኮሚቴ ጥናት ዉስጥ ሲዳማ አለመካተቱን ለዚህ እንደ አንድ ማስረጃ አንስተዋል፡፡ “የሲዳማ ህዝብ ህዝበ ዉሳኔ ያደረገው ብቻውን ለመደራጀት እንጂ ከሌሎች ጋር በጋራ ለመደራጀት አይደለም” ያሉት አቶ ገነነ “ሌሎች ዞኖች እና ወረዳዎች ከሲዳማ ጋር ይደራጁ ከተባለ ሌላ ተጨማሪ ህዝበ ዉሳኔ ሊደረግ ይገባል ማለት ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ “ይህ ደግሞ ሲዳማ የራሱን ፍላጎት የወሰነ በመሆኑ ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ ነው” ብለዋል፡፡ ባጠቃላይ ሲዳማን ለብቻው በክልልነት ከማደራጀት ዉጭ በአማራጭነት የተያዘ ዕቅድ እንደሌለና ከዚህ በተለየ መልኩ የሚሰራጩ መረጃዎች የፈጠራ አሉባልታዎች እንደሆኑ ደምድመዋል፡፡
የሲዳማን ዞን በክልል ደረጃ ለማደራጀት ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ዞኑ የኢትዮጵያ 10ኛው ክልል ለመሆን በሕዝበ ውሳኔው ለመሳተፍ ከተመዘገበው ህዝብ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆነውን ፣ማለትም 98.51 በመቶ ድምጽ ማግኘቱን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወቅቱ መግለጹ ይታወቃል፡፡