የቃልኪዳን ተስፋዎች…
በኢትዮጵያ በዐይን ብሌን ለጋሾች እጦት ምክንያት የበርካቶችን ዕይታ ለመመለስ ሳይቻል ቀርቷል
ከ10 ዓመት በፊት የተደረገ ጥናት ከ300 ሺህ በላይ አይነ ስውራን በኢትዮጵያ እንዳሉ ያመለክታል
ቃልኪዳን ትባላለች፡፡ የ11 ዓመት ህጻን ስትሆን የተወለደችው በአማራ ክልል መርጦ ለማርያም ነው። እስከ አራት ዓመቷ ድረስ ትንሽ ትንሽ ማየት ትችል እንደነበር እናቷ ወይዘሮ አዲስ ያስታውሳሉ። ቀስ በቀስ ግን ሙሉ ለሙሉ ማየት ያቆመችው ህጻን ቃልኪዳን ያለ እናቷ እርዳታ ምንም ነገር ማድረግ አልቻለችም።
“ልጄ ማየት ካለመቻሏ በተጨማሪ እንደ እድሜ እኩዮቿ ትምህርት ቤት አለመሄዷ ከምንም በላይ ይቆጨኛል” የሚሉት ወይዘሮ አዲስ ልጄ ከእኩዮቿ ጋር ስትጫወት፣ ትምህርት ቤት ስትሄድ እና እንደ ልቧ መንቀሳቀስ ስትችል ማየት የሁልጊዜ ምኞቴ ነው ሲሉ ይናገራሉ።
ለ80 አካል ጉዳተኞች ሰው ሰራሽ አካል በነጻ የሰራው በጎ ፈቃደኛ
የያዝነው ሳምንት የዓለም እይታ ቀን የሚከበርበት ሳምንት ነው። አል ዐይን አማርኛ ይሄንን ምክንያት በማድረግ ሰሞኑን ወደ አይን ሆስፒታሎች ጎራ ብሎ ተመልክቷል። በዚህ ጊዜ ነበር ቃል ኪዳን በእናቷ ረዳትነት ህክምና ለማግኘት በዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል የዓይን ህክምና ለማግኘት ወረፋ ስትጠባበቅ ያገኛት።
“ምንም ነገር አይታየኝም ነጭ ነገር ብቻ ነው የሚታየኝ” የምትለው ህጻን ቃልኪዳን ህክምናውን አግኝታ ስትድን “መጀመሪያ እናቴን እና ቤታችንን ማየት እፈልጋለሁ” ስትልም ነግራናለች።
እናቷ ወይዘሮ አዲስ በበኩሏ “ልጄ ማየት ባለመቻሏ ከጎረቤት እኩዮቿ ጋር መጫወት አትችልም፤ ልጆቹ ትወድቅብናለች በሚል አብረዋት ለመጫወት ፈቃደኛ አይደሉም፤ያኔ ታለቅሳለች። የእኔ የሙሉ ጊዜ ስራዬ እሷን መከታተል እና ከአደጋ መጠበቅ ሆኗል” ሲሉም ተናግረዋል።
“የልጄን አባት ጨምሮ በአካባቢያችን ማህበረሰብ የዓይን እይታ አንዴ ከታጣ በኋላ መዳን አይችልም የሚል የጸና አመለካከት አለ” የሚሉት ወይዘሮዋ እኔ ግን ልጄ ህክምና ቢደረግላት ልትድን ትችላለች የሚል ዕምነት ስለነበረኝ ወደዚህ ሆስፒታል ይዣት መጣሁ ሲሉ ያክላሉ።
ለህጻን ቃልኪዳን እና ለእናቷ መልካም እድል ተመኝተን ከህክምና በኋላ እንደምንገናኝ ተስፋ አድርገን ተለያየን።
ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ወደ ሆስፒታል ስንመለስ በዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል የአይን ብሌን ንቅለ ተከላ ሐኪም ዶክተር መነን አያሌው ህጻን ቃልኪዳን ጋር አገኘናቸው።
ህጻን ቃልኪዳን የግራ አይኗ ተሸፍኖ አገኘናት እና ህክምናው እንዴት ነበር ስንል ጠየቅናቸው።
ዶ/ር መነንም ህጻን ቃልኪዳን ከተወለደች ጀምሮ የአይን ብሌኗ ውስጠኛው ክፍል መጎዳቱ እይታዋን ለማጣቷ ምክንያት መሆኑን ተከትሎ የአይን ብሌን ንቅለ ተከላ ህክምና እንደተደረገላት ነገሩን።
ለህጻን ቃልኪዳን የአይን ብሌን ንቅለ ተከላ የተደረገላት ከበጎ ፈቃደኛ ሰው በተለገሰ የዐይን ብሌን መሆኑንም አጫውተውናል።
በግላቸው 326 ገደማ የልብ ቀዶ ጥገናዎችን ያደረጉት ኢትዮጵያዊ ሐኪም
“ዛሬ የብሌን ንቅለ ተከላ ያደረግንላት ህጻን ቃልኪዳን ለአንድ አይኗ ብቻ ነው” የሚሉት ዶ/ር መነን ለሁለተኛው ዐይኗ ለጋሽ እንደተገኘ ንቅለ ተከላ ይደረግላታል ብለዋል፤ ይ መቼ ሊሆን እንደሚችል አለመታወቁን በማከል።
ለቃልኪዳን የተደረገላት የዐይን ብሌን ንቅለ ተከላ በማግስቱ በፋሻ የታሸገው አይኗ የሚፈታበት ነው እና በጠዋቱ ወደ ሆስፒታሉ አመራን።
ህጻን ቃልኪዳን እና እናቷ በጠዋት ነበር ሆስፒታሉ የተገኙት። ከትንሽ ህመም ውጪ የተለየ ህመም እንዳልተሰማት እና ሌሊቱን ተኝታ ማደሯን ነገረችን።
እኛም የአይን ንቅለ ተከላ የተደረገበት እና የተጠቀለለው አይኗ በሀኪሞች ሲፈታ እና እይታዋን ሲያረጋግጡ ተመለከትን።
ህጻን ቃል ኪዳንም በአንድ ዐይኗ በምታገኛት ብርሀን እናቷን፣ ሀኪሞችን እና ወረፋ የሚጠብቁ ታካሚዎችን በደስታ ለመመልከት ቻለች፡፡ ይህ ሁሉንም ያስደሰተ ነበረ፡፡
በኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩና ማየት የማይችሉ ሰዎች አሉ፡፡ የዐይን ብሌን ንቅለ ተከላ ተደርጎላቸው እይታቸው የሚመለሱ ሰዎች ቁጥር ግን ቀላል እንዳልሆነም ብሔራዊ የዐይን ባንክ መረጃ ያስረዳል።
ይሁንና ብዙ ሰዎች የዐይን ብሌን ለመለገስ ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ የግንዛቤ ችግርም አለ፡፡ ይህ በመሆኑ የጠፋ ብርሃናቸውን መልሰው ለማግኘት ይችሉ የነበሩ በርካቶች እይታቸው ሳይመለስ ህይወታቸው አልፏል፤ አሁንም የሚያልፉ አሉ።
የጉዳዩን አሳሳቢነት የሚያነሱት ዶ/ር መነን አያሌውም የዐይን ብሌን የሚለግስ በመጥፋቱ ምክንያት ቀደም ሲል የሚያዙ ቀጠሮዎች በተደጋጋሚ እንደሚሰረዙ እና ይህን ለማድረግ እንደሚገደዱ ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ አሁን ላይ ምን ያህል ዐይነ ስውራን ሰዎች እንዳሉ የሚያሳይ የቅርብ ጊዜ ጥናት ባይኖርም ከ10 ዓመት በፊት በተደረገ ጥናት ግን ከ300 ሺህ በላይ ሰዎች እንዳሉ የብሔራዊ የዐይን ባንክ መረጃ ያስረዳል።
የብሔራዊ የዐይን ባንክ ዳይሬክተር ወ/ሮ ለምለም አየለ በበኩላቸው ሰዎች ህይወታቸው ካለፈ በኋላ የዐይን ብሌናቸውን እንዲለግሱ የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ነን ይላሉ፡፡
ይሁንና ብዙ ሰዎች ጉዳዩን ከሀይማኖት ጋር በማገናኘት እና በሌሎች የአመለካከት ችግሮች ምክንያት የዐይን ብሌናቸውን የሚለግሱ በጎ ፈቃደኛ ሰዎች ጥቂት ናቸው እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ።
በኢትዮጵያ ልብ እና ሳንባ ቆመው የሚሰጠው ቀዶ ህክምና
እስካሁን ድረስ ከበጎ ፈቃደኞች በተለገሰ የዐይን ብሌን የ2 ሺህ 523 ሰዎችን እይታ ለመመለስ መቻሉንም ወ/ሮ ለምለም ገልጸዋል።
የዐይን ብሌን የሚለገሰው ከህልፈተ ህይወት በኋላ ነው፡፡ የምትለገሰውም ብሌን የምትባለው የዐይን ክፍል ብቻ ናት፡፡በመሆኑም ሰዎች የዐይን ብሌናቸውን ቢለግሱ ከሀይማኖትም ሆነ ከሌሎች ሁኔታዎች ጋር የሚጋጭ ምንም አይነት ነገር እንደሌለው ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡
ብሔራዊ የዐይን ባንክ አዲስ አበባን ጨምሮ በአማራ፣ በደቡብ፣ በትግራይ እና በኦሮሚያ ክልሎች ቅርንጫፎቹን ከፍቶ በመስራት ላይ ነው፡፡ ሆኖም በአዲስ አበባ ብቻ ነው የዐይን ብሌን ከበጎ ፈቃደኞች እየሰበሰበ ያለው።