ሲንጋፖር አምስት አደገኛ እጽ አዘዋዋሪዎችን በስቅላት መቅጣቷ ተገለጸ
በሲንጋፖር የአደገኛ እጽ ሲያዘዋውር የተገኘ ግለሰብ ታንቆ እንዲገደል ህጉ ያስገድዳል
አምንስቲ ኢንተርናሽናል የሲንጋፖር መንግስትን ድርጊት አውግዟል
ሲንጋፖር በአራት ወራት ውስጥ አምስት አደገኛ እጽ አዘዋዋሪዎችን በስቅላት መቅጣቷ ተገለጸ።
የኤስያዋ ሲንጋፖር ባለፉት አራት ወራት ውስጥ አምስት አደገኛ እጽ አዘዋውረዋል በሚል የጥፋተኝነት ውሳኔ የተላለፈባቸውን ተከሳሾች ታንቀው እንዲሞቱ ማድረጓ ተገልጿል።
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ተቋም እንደገለጸው ሲንጋፖር በዜጎች ላይ የምትፈጽመውን የሞት ፍርድ እንድታቆም ጠይቋል።
ሲንጋፖር በሀገሯ እየተስፋፋ የመጣውን የአደገኛ እጽ ዝውውር ለማስቆም በአዘዋዋሪዎች ላይ የሞት ፍርድ ማስተላለፍ የሚያስችል ህግ አጽድቃለች።
በዚህ ህግ መሰረት ባለፉት አራት ወራት ውስጥ አምስት አደገኛ እጽ ዝውውር ፈጽመዋል በሚል ተከሰው የጥፋተኝነት ውሳኔ የተላለፈባቸው ተከሳሾችን ታንቀው እንዲገደሉ አድርጋለች።
ዛሬ ማለትም አርብ ረፋድ ናዛሪ ላጅም የተባለ ግለሰብ 34 ግራም ዕጽ ይዞ በመገኘቱ በስቅላት እንዲሞት መደረጉን አምንስቲ ኢንተርናሽናል በድረገጹ አስታውቋል።
የሲንጋፖር መንግስት ውሳኔ የተመድን ሰብዓዊ መብት ድንጋጌ ስር የተቀመጠውን ማንኛውም ሰው በህይወት የመኖር መብትን የሚጻረር እንደሆነ አምንስቲ ተችቷል።
ሲንጋፖርን ጨምሮ 110 የዓለማችን ሀገራት የሞት ፍርድን የሚፈቅድ ህግ ሲኖራቸው አራት ሀገራት ደግም ከአደገኛ እጽ ይዞ የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ የስቅላት ፍርድ የሚቀጣ የግዴታ ህግ አላቸው ተብሏል።