ሲንጋፖር እና ዙሪክ የአለም ውድ ከተሞች ሆኑ
ሪፖርቱ እንደገለጸው የአለም የኑሮ ውድነት ቀውስ የመቀነስ አዝማሚያ አያሳይም
በበርካታ መደቦች ባስመዘገበችው ከፍተኛ ዋጋ ምክንያት ሲንጋፖር ባለፉት ዘጠኝ አመታት በውድነት አንደኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች
ሲንጋፖር እና ዙሪክ የአለም ውድ ከተሞች መሆናቸው ተገለጸ።
ሲንጋፖር እና ዙሪክ፣ ጀኔቫን፣ ኒውዮርክን እና ሆንግ ኮንግን በማስከተል በዚህ አመት የአለም ውድ ከተሞች መሆናቸውን ሮይተርስ የኢኮኖሚስት ኢንተሊጀንስ ዩኒት ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሶ ዘግቧል።
ሪፖርቱ እንደገለጸው የአለም የኑሮ ውድነት ቀውስ የመቀነስ አዝማሚያ አያሳይም።
እንደ ሪፖርቱ ከሆነ በአማካኝ ሲታይ በብዛት ጥቅም ላይ በሚውሉት 200 የፍጆታ ቁሳቁሶች እና አገልግሎቶች ላይ የ7.1 በመቶ አመታዊ የዋጋ ግሽበት ታይቷል። ነገርግን ባለፈው አመት በክብረወሰንነት ከተመዘገው 8.1 በመቶ ጭማሪ ጋር ሲነጻጸር ትርጉም ያለው ቅናሽ አሳይቷል።
በበርካታ መደቦች ባስመዘገበችው ከፍተኛ ዋጋ ምክንያት ሲንጋፖር ባለፉት ዘጠኝ አመታት በውድነት አንደኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። መንግስት በመኪና ቁጥር ላይ በሚያደርገው ቁጥጥር ምክንያት በከተማዋ የትራንስፖርት ዋጋ በጣም ውድ የሚባል ነው።
የልብስ፣ የመዝናኛ ቤት እና የመጠጥ ወጭም እጅግ ውድ ነው።
የዙሪክ የኑሮ ውድነት በስዊስ ፍራንክ መጠንከር እና የሬስቶራንት፣ የመዝናኛ እና የቤት ፍጆታ ውጭዎች ከፍተኛ በመሆኑ ምክንያት የመጣ መሆኑን በሪፖርቱ ተገልጿል።
ጄኔቫ እና ኒውዮርክ ተያይዘው ሶስተኛ ደረጃ ሲይዙ ሆንግ ኮንግ እና ሎስ አንጀለስ በተከታታይ አራተኛ እና አምስተኛ ደረጃ ይዘዋል።
እስያ ከሌላው ቀጣና አንጻር ሲነጻጸር በአንጻራዊነት ዝቅተኛ የዋጋ ጭማሪ አሳይቷል።
የቻይና አራቱ ከተሞች-ናንጄንግ፣ ዉዥ፣ ዳሊያን እና ቤጅንግ ከነበሩበት ደረጃ ዝቅ ብለዋል።