የተመድ የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼል ባችሌት “ሁለተኛ የስልጣን ዘመን እንደማይፈልጉ” አስታወቁ
የባችሌት ያልተጠበቀ ውሳኔ ተከትሎ በጄኔቫ ምክር ቤት ውስጥ “ማጉረምረም” ነበር ተብሏል
ባችሌት ዓለም አቀፉ ድርጅትን በሁለተኛ የስልጣን ዘመን ለምን መምራት እንዳልፈለጉ በግልጽ ያሉት ነገር የለም
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ባችሌት ሁለተኛ የስልጣን ዘመን እንደማይፈልጉ አስታወቁ።
ባችሌት ይህን ውሳኔ ያስታወቁት መቀመጫው በጄኔቫ ላደረገው የሰብአዊ መብት ምክር ቤት ሰፋ ያለ ንግግር ባደረጉበት በዛሬው እለት ነው።
“የከፍተኛ ኮሚሽነርነትየስልጣን ዘመኔ ሊጠናቀቅ እየተቃረበ ነው፤ እናም ይህ 50ኛ የምክር ቤቱ ጉባኤ የመጨረሻ ይሆናል” ሲሉም ተደምጠዋል።
ለተመድ ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የቅርብ ሰው እንደሆኑ የሚነገርላቸው የቀድሞ የቺሊ ፕሬዝዳንት ባችሌት “ዜና” በርካቶች ያልጠበቁት እንደነበር ሮይተርስ ዲፕሎማቲክ ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።
ኮሚሽነሯ ያልተጠበቀውን ውሳኔ ይፋ ባደረጉበት ወቅት በጄኔቫ ምክር ቤት ውስጥ ማጉረምረም ነበረም ነው የተባለው። ባችሌት ዓለም አቀፉ ድርጅትን በሁለተኛ የስልጣን ዘመን ለምን መምራት እንዳልፈለጉ በግልጽ ያሉት ነገር የለም።
ይሁን እንጂ፤ ባችሌት የዓለም አቀፉን ድርጅት ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት ለመምራት ያለፈለጉበት ምክንያት የቅረቡ የቻይና ጉብኝታቸውን ተከትሎ ከምዕራባውያን እና የመብት ተሟጋች ተቋማት የተሰነዘረባቸው ትችት ሊሆን እንደሚችል እየተገለጸ ነው።
ባችሌት ከሁለት ሳምንታት በፊት በቻይና ምዕራባዊው ከፍል በምትገኘውና የበርካቶች ማጎርያና የሲቃይ ማእከል እንደሆነች በሚነገርላት የዢንጂያንግ ግዛት የስድስት ቀናት ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
የባችሌት ጉብኝት አንድ የተመድ ከፍተኛ የስብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ቻይና ሲጎበኙ ከ17 ዓመታት በኋላ የተደረገ የመጀመርያው መሆኑ ነው።
ያም ሆኖ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች እና ምዕራባውያን ሀገራት የባችሌት ጉዞ በቻይና የመብት ጭላንጭል እንዳለ ማሳያ አድርጋ ለማስረጃነት ልትጠቀምበት ትችላለች የሚል ነገር በወቅቱ አስጨንቋቸው እንደነበር አይዘነጋም።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ በወቅቱ በሰጡት መግለጫ "በእንዲህ አይነት ሁኔታ ውስጥ መጎብኘት ስህተት ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።
የሂዩማን ራይትስ ዎች ዋና ዳይሬክተር ኬኔት ሮትም እንዲሁ የኮሚሸነሯ የቻይና ጉብኝት “ያልታሰበ አደጋ” ሲሉ ነበር የጠሩት።
ይሁን እንጅ ባችሌት ለተቺዎቻቸው በወቅቱ በሰጡት ምልሽ “ግድ የላችሁም ቤጂንግ የጸረ- ሽብር ፖሊሲዎቿን እንድትገመግምና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት መስፈርቶችን ያሟሉ መሆናቸውን እንድታረጋግጥ አስስቤያታለሁ” ብለው ነበር።
በቻይና ቆይታየ “የጸረ-ሽብርተኝነት ፖሊሲን እና የጥላቻ እርምጃዎችን አተገባበር በተመለከተ ያሉኝን ጥያቄዎችን እና ስጋቶችን አንስቻለሁ ፣በተለይም በኡዩጉሮች እና በሌሎች አናሳ ሙስሊም ወገኖች መብት ላይ ስላለው ተጽእኖ አንስቻለሁ” ማለታቸውም የሚታወስ ነው።
ያም ሆኖ አሜሪካን ጨምሮ በወቅቱ የተሰሙ የምዕራባውያን የተቃውሞ ድምጾች ባችሌት አሁን ለደረሱበት የመጨረሻ ውሳኔ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ እየተባለ ነው።