“ጆ ባይደን አሜሪካውያንን ስቃይ ለመጨመር የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ነው” ያሉት የኋይት ኃውስ ቃል አቀባይ
ቃል አቀባይዋ ንግግር “የአፍ ወለምታ” እንደሆነ ተነግሯል
ጆ-ባይደን ከወራት በፊት “ፑቲን ስልጣን ላይ መቆየት አይችሉም” ያሉበትና ማስተካከያ የሰጡበት ንግግራቸው ይታወሳል
ከመሪዎች ምላስ ሚወጣው ቃልና ንግግር በተደራሲያን ዘንዳ በፖሊሲ ደረጃ ሊወሰድ የሚችል ቁም ነገር መሆኑ እሙን ነው።
በዓለማችን በሚናገሯቸው ንግግሮች ከፍተኛ ማዕበል የሚፈጥሩ መሪዎች እንዳሉ ሁሉ፤ በሚናገሩት ቃል ከራሳቸው አልፎ ለዜጎቻቸው ሌላ መዘዝ የሚያስከትሉ መሪዎች ማየት አሁን አሁን የተለመደ ነው።
የወቅቱ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከሳቸው በፊት ከነበሩት አወዛጋቢው መሪ ዶናልድ ትራምፕ የተሻለ የተግባቦት ክህሎት እንዳላቸው ባያከራክርም፤ በተለያዩ ጊዜያት በተናገሯቸው ንግግሮች የአሜሪውያንን ሲቃይ እንዳበዙ ይነሳል።
በተለይም ባይደን ከሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ በክሬምሊን ሰዎች ላይ የሰነዘሯቸው ትችቶች ከዛም ባለፈ በሩሲያ ላይ የጣሏቸው ማእቀቦች በተዘዋዋሪም ቢሆን የአሜሪካውያን ህይወት ሲያዛቡ ተስተውሏል።
የምጣኔ ሀብት መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ አሁን ላይ በአሜሪካ ያለው የዋጋ ግሽበት ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ፈተና ሆኖ ቀጥሏል 8 ነጥብ 6 በመቶ ደርሷል። ይህም ከታህሳስ 1981 ወዲህ ከፍተኛው ደረጃ ላይ ደርሷል፣ የቤንዚን ዋጋም እንዲሁ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በጋሎን ከ5 ዶላር በላይ ጨምሯል።
በዩክሬን ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረ በኋላ ምዕራባውያን ሀገራት በሞስኮ ላይ ማዕቀብ የጣሉ ሲሆን፤ ይህም በአሜሪካ እና አውሮፓ ውስጥ የአቅርቦት ሰንሰለት መቋረጥ እና የኢኮኖሚ ችግሮች አስከትሏል።
ለዚህ ሁሉ ደግሞ ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን የወሰድዋቸው እርምጃዎችና “በአፍ ወለምታ የተናገሩዋቸው” ቃላቶች መሆናቸው ይገለጻል።
የአሜሪካ መሪዎች ስህተት ግን በጆ-ባይደን ብቻ የታጠረ አይደለም። የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ካረን ዣን ፒየር የወቅቱ ስህተት በርካታ የመገናኛ ብዙሃን እየተቀባቡለት ያለ ጉዳይ ሆኗል።
ባይደን አስተዳደር በከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ ምክንያት እየተሰቃዩ ያሉትን ቤተሰቦችን ለመደገፍ ስለሚወስዳቸው እርምጃዎች ተጠይቀው “ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አሜሪካውያን ስቃይ ለመጨመር የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ነው” የሚል ምላሽ የሰጡበት አጋጣሚ አነጋገሪ ሆኗል።
ይሁን እንጅ “በአፍ ወለምታ” ስህተት እንደሰሩ የገባቸው ቃል አቀባይዋ ወዲያውኑ ስህተታቸው አርመዋል።
ፒየር “ፕሬዚዳንቱ በከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ ምክንያት ጫና ውስጥ ገቡት አሜሪካውያንን ሲቃይ ለማቃለል የቻሉትን ሁሉ እርምጃዎች እየወሰዱ ነው” የሚል ማስተካከያም አድረገዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን ባሳለፍነው ወርሃ መጋቢት በፖላንድ በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉት ስደተኞች መጎብኘታቸው ይታወሳል።
በዚህ ወቅት ፕሬዝዳንቱ “የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ስልጣን ላይ መቆየት አይችሉም” ማለታቸው በወቅቱ አነጋጋሪና የአሜሪካ ወዳጆች ሳይቀሩ ያወገዙት ንግግር እንደነበር አይዘነጋም።
ይሁን እንጅ የተናገሩት ነገር ስህተት እንደሆነ ገባቸው ባይደን በዋይት ሃውስ በኩል በሰጡት የእርምት መግለጫ ፤ይቅርታ ፑቲን ስልጣን ላይ አይቆይም ያልኩት ከተመለከትኩት አሳዛኝ ድርጊት እንጻር እንጅ “የስርዓት ለውጥ” ማለቴ አይደለም የሚል ማስተባበያ አዘል ማስተካከያ ሰጥተዋል።
ፕሬዝዳነቱ የአሜሪካ ጦር መጀመሪያ ወደ ዩክሬን በመግባት አስፍላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ካሉ በኋላ መልሰው የአሜሪካ ጦር ወደ ዩክሬን እንደማይገባ የተናገሩበት አጋጠሚም አወዛጋቢ ሆኖ አልፈዋል።
እንደ ኒውዮርክ ፖስት ዘገባ ከሆነ፤ የባይደን አስተዳደር ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ዋይት ሃውስ፤ የባይደን አፍ ወለምታ ንግግሮች በማስተካከል የተጠመደ ይመስላል።