ሞስኮ፤ “በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በቦምብ የምትደበድብ ሀገር ፑቲንን የጦር ወንጀለኛ የማለት ሞራል የላትም” ብላለች
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን፤ የሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን “የጦር ወንጀለኛ ናቸው” ብለው መናገራቸው ተቀባይነት እንደሌለው ሞስኮ ገለጸች። የክሬምሊን ቃል አቀባይ፤ ባይደን የተናገሩት ንግግር ተቀባይነት የሌለውና ይቅር የማይባል ነው ብለዋል።
ጆ ባይደን ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ ቭላድሚር ፑቲን የሀገራቸው ጦር ወደ ዩክሬን አስገብተው በተፈጸመው ክስተት “የጦር ወንጀለኛ ናቸው” ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን ሩሲያ ደግሞ ይህንን ውድቅ አድርጋዋለች።
የሩሲያ ቤተ መንግስት (ክሬምሊን) ቃል አቀባይ ድሚትሪ ፔስኮቭ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ፕሬዘዳንት ባይደን የተናገሩትን ንግግር “ተቀባይነት የሌለና መቸም ይቅር የማይባል ነው” ብለዋል።
ቃል አቀባዩ ፤ በመላው ዓለም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በቦምብ የምትደበድብ ሀገር የሩሲያን ፕሬዘዳንት የጦር ወንጀለኛ የማለት ሞራል የላትም ሲሉ ለሩሲያ ዜና አገልግሎት ታስ ተናግረዋል።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ( ኔቶ) ን ለመቀላቀል ፍላጎት ማሳየቷን ተከትሎ ከሶስት ሳምንት በፊት የሩሲያ ጦር “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” በሚል ወደ ዩክሬን መግባቱ ይታወሳል።
በዚህም ምክንያት በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል ግልጽ ጦርነት የተጀመረ ሲሆን ከሶስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሀገራቸውን ለቀው ወደ ጎረቤት ሀገራት መሰደዳቸውን ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት በሪፖርት ገልጿል።
የዩክሬን ፕሬዘዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ወደ ዩክሬን የገቡ የሩሲያ ወታደሮች እጅ እንዲሰጡ ማሳሰባቸው ይታወሳል።