በቬትናም “አደገኛ ነው” የተባለ አዲስ የኮቪድ 19 ዝርያ ተገኘ
አዲሱ የቬትናም የኮቪድ 19 ቫይረስ ዝርያ የብሪታንያና የህንድ የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች ውህድ ነው
አዲሱ ዝርያ በአየር አማካኝት በፍጥነት የሚዛመትና “አደገኛ” መሆኑን የቬትናም ጤና ሚኒስቴር ገልጿል
ቬትናም እስካሁን ካሉት የተለየ አዲስ እና “አደገኛ” የሆነ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ በሀገሯ ውስጥ መገኘቱን አስታወቀች።
በቬትናም የተስተዋለው የኮቪድ 19 ቫይረስ ዝርያ በብሪታንያ እና በህንድ የተገኙ የቫይረሱ ዝርያዎች ውህድ ሲሆን፣ በአየር አማካኝት በፍጥነት የሚዛመት መሆኑንም የቬትናም ጤና ሚኒስትር ነጉየን ታህን ሎንግ አስታውቀዋል።
ይህ የኮቪድ 19 ዝርያ ከዚህ ቀደም ከነበሩት የበለጠ ተላላፊ መሆኑን ያስታወቁት የጤና ሚኒስትሩ፤ “በጣም አደገኛ” ሲሉም ገልጸውታል።
ሚኒስትሩ እንዳሉት ፣ አዲሱ የቬትናም የኮቪድ 19 ዝርያ ሊገኝ የቻለው በአንድ በቅርቡ ታሞ ወደ ህክምና ማእከል በሄደ ግለሰብ ላይ በተደረገ ምርመራ ነው።
ለአዲሱ የቫይረሱ ዝርያ መለያ ኮድ ገና ያልተሰጠው መሆኑንም ሚኒስትሩ አክለው ገልጸዋል።
በህንድ የተስተዋለው የኮቪድ 19 ዝርያ ‘B.1.617.2’ የሚል መለያ ኮድ የተሰጠው ሲሆን ፣ በብሪታንያ የተገኘው የኮቪድ 19 ዝርያ ደግሞ ‘B.1.1.7’ የሚል መለያ ኮድ አለው።
በቬትናም የተገኘው የብሪታንያ እና የህንድ ዝርያ ውህድ የሆነው የኮቪድ 19 ዝርያ ፣ በሰዎች ላይ የከፋ ጉዳት ስለማድረሱ እስካሁን የተለየ ነገር የለም።
ይሁን እንጂ ልክ እንደ ዋነኛው የኮቪድ 19 ዝርያ እድሜያቸው በገፋ ሰዎች እና ተጓዳኝ በሽታ ባለባቸው ሰዎች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ እንደሆነ ነው ተመራማሪዎች የሚናገሩት።