የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጁ ግዛቶች አምስት ደርሰዋል
ከዳቦ ጥያቄ እና ከኑሮ ውድነት ጋር በተያያዘ በሱዳን የተጀመረው የተቃውሞ እንቅስቃሴ አሁንም በተለያዩ ግዛቶች እንደቀጠለ ነው፡፡ ይህንን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያውጁ ክልልሎችም እየጨመሩ ይገኛሉ፡፡
ሁለት ተጨማሪ ግዛቶች በዛሬው ዕለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይፋ አድርገዋል፡፡ ከነዚህም አንዱ የሲናር ግዛት ሲሆን የግዛቱ አስተዳዳሪ አል-ማሂ መሀመድ ሱሌይማኒ እንዳሉት ፣ አዋጁ ሁሉም የጸጥታ አካላት በየደረጃቸው ያለውን የመጨረሻ ስልጣን በመጠቀም የገበያ ስፍራዎችን እንዲሁም የመንግስት እና የህዝብ ተቋማትን ከጥፋት እንዲታደጉ ያዛል፡፡
በግዛቱ የሚገኙ ታላላቅ ሰዎች የቀድሞው ስርዓት አቀንቃኞች እና ደጋፊዎች የሚገኙበትን እንዲጠቁሙ እንዲሁም እንቅስቃሴያቸውን እንዲከታተሉም በአስቸኳይ አዋጁ ተደንግጓል፡፡
በሀገሪቱ ዘረፋ እና ቅሚያ እንዲፈጸም በማድረግ የተወነጀሉትን የቀድሞው ስርዓት ናፋቂዎች ተከታትለው እንዲቆጣጠሯቸው የጸጥታ ኃይሎችም ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡
በምዕራብ ኮርዶፋን ግዛትም በተመሳሳይ የአስቸኳይ ጊዜ የታወጀ ሲሆን ከቀኑ 10 ሰዓት እስከ ማለዳው 12 ሰዓት የእንቅስቃሴ እገዳ ተጥሏል፡፡ የሱዳን ዜና ወኪል እንደዘገበው እገዳው የጸጥታ ኃይሎችን ፣ የመብራት ፣ የውሃ እና የባንክ ባለሙያዎችን አያካትትም፡፡
በትናንትናው ዕለት በሦስት ግዛቶች ፣ ማለትም በደቡብ እና በሰሜን ዳርፉር እንዲሁም በሰሜን ኮርዶፋን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ይታወሳል፡፡
ከዳቦ ፣ ከዱቄት ፣ ከነዳጅ እና ከምግብ ማብሰያ ጋዝ ጥያቄ ጋር በተያያዘ የተጀመረው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ባለፉት ጥቂት ቀናት ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን የተለያዩ ዘረፋዎች እና የንብረት ውድመቶችም ተፈጽመዋል፡፡