![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/06/252-210243-whatsapp-image-2025-02-06-at-8.01.47-pm_700x400.jpeg)
ሮናልዶ በቀጣዮቹ ሁለት ወይም ሶስት ዓመታት ውስጥ ኳስ መጫወት ሊያቆም እንደሚችል ተናግሯል
ፖርቹጋላዊው የእግር ኳስ ኮከብ ክስርስቲያኖ ሮናልዶ “እድሜህ ከ35 ዓመት ካለፈ በኋላ እግር ኳስን መጫወት ስጦታ ነው” ነው ብሏል።
ክስርስቲያኖ ሮናልዶ በትናንትናው እለት 40ኛ ዓመት የልደት በዓሉን ያከበረ ሲሆን፤ ስለ እግር ኳስ ህይወቱ እና ስለ ወደፊት እቅዱ ከካናል 11 ጋር ቆይታ አድርጎ ነበር።
በአሁኑ ወቅት በሳዑዲ ፕሮ ሊግ ውስጥ ለአል ናስር የእግር ኳስ ክለብ የሚጫወተው ፖርቹጋላዊው የእግር ኳስ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በትናንትናው እለት 40 ዓመት ሞልቶታል።
ሮናልዶ አሁን ላይ እግር ኳስ መጫወቴን ብቻ ነው የማውቀው፤ የሆነ ቀን ላይ የሚያበቃት ቀን ሊመጣ ይችላል፤ ያ ጊዜ በቀጣዮቹ አንድ ወይም ሁለትና ሶስት ዓመታት ውስጥ ሊከሰት ይችላል ብሏል።
ሆኖም ግን እድሜው እና አቅሙ እስከፈቀደ ድረስ የእግር ኳስ ሜዳዎች ላይ ተዓምር መስራቱን እንደሚቀጥል ተናግሯል።
በብሄራዊ ቡድን ውስጥ እንድጫወት ያድረገኝ የእግር ኳስ ፍቅር ነው ያለው ሮናልዶ፤ የሆነ ቀን ላይ ሊቆም ይችላል፤ ለዚህም ነው በእግር ኳስ መዝናናትን የምመርጠው ብሏል።
በብሄራዊ ቡድኑ ጥሪ ከቀረበለት በ2026 የዓለም ዋንጫ ላይ ለሀገሩ ተሰልፎ የመጫወት እንደሚፈልግ የተናገረ ሲሆን፤ ከተሳካለለት 6ኛ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎው ይሆናል።
እግር ኳስን ካቆመ በኋላም የራሱ የሆኑ የእግር ኳስ ክለቦች እንዲኖሩት እንደሚፈልግም ተናግሯል።
ከከርስቲያኖ የዋንጫ ማደርደሪያ ሳጥን ላይ የሚጎድለው የአለም ዋንጫ ነው፤ ሮናልዶ በ2026 የአለም ዋንጫ በሚዘጋጅበት ጊዜ እድሜው 41 አመት ይሞላዋል፡፡
ከሀገሩ ብሔራዊ ቡድን ጋር የአለም ዋንጫን ማንሳት የሁልጊዜ ምኞቱ እንደሆነ የሚናገረው ሮናልዶ በቀጣዩ አመት በሚከናወነው አለምአቀፋዊ ውድድር ላይ በሚኖረው ተሳትፎ ዙሪያ እርግጠኛ የሆነ መረጃ አልወጣም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በተለያዩ ውድድሮች ለፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን ተሰልፎ ባደረጋቸው ውድድሮች በ217 ጨዋታዎች 135 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡
በክለቦች የሚኖረው የእግር ኳስ ህይወት በሳኡዲ አረብያው አልናስር ሊጠናቀቅ እንደሚችል ፍንጭ የሰጠው ሮናልዶ ያስቆጠራቸውን ግቦች ወደ አንድ ሺህ ከፍ ማድረግ እንደሚፈልግ ተናግሯል፡፡
አልሂላል እና አል ኢትሀድ በጋራ እየመሩት በሚገኝው የሳኡዲ ሊግ ከመሪዎቹ በአምስት ነጥብ ዝቅ ብሎ በሚገኝው አልናስር ሮናልዶ በአጠቃላይ በተሰለፈባቸው 94 ጨዋታዎች 85 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡