ዩክሬን የሩሲያ የጥቁር ባህር መርከቦች አዛዥን መግደሏን አስታወቀች
ባለፈው ሳምንት በሴቫስታፖል በፈጸመችው የሚሳኤል ጥቃት 34 ሰዎች መገደላቸውንም ነው የዩክሬን ልዩ ሃይል የገለጸው
ሞስኮ ግን የመርከብ አዛዡ ስለመገደሉ ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ አልሰጠችም
ዩክሬን ባለፈው ሳምንት በሩሲያ የጥቁር ባህር መርከቦች ማዘዣ ጣቢያ በፈጸምኩት ጥቃት 34 ሰዎች ተገድለዋል አለች።
ከሟቾቹ ውስጥም የሩሲያ የጥቁር ባህር መርከቦች አዛዡ አድሚራል ቪክቶር ሶኮሎቭ ይገኙበታል ተብሏል።
የዩክሬን ልዩ ሃይል የአዛዡን ስም በመግለጫው ውስጥ ባይጠቅስም የዩክሬን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አማካሪ አንቶን ግራሽቼንኮ የአድሚራሉን ስምና ምስል በኤክስ(ትዊተር) ገጻቸው ላይ አጋርተዋል።
በክሬሚያዋ ሴቫስታፖል ከተማ በተፈጸመው ጥቃት አድሚራል ቪክቶርን ጨምሮ 34 ስብሰባ ላይ የነበሩ አመራሮች መገደላቸው ተገልጿል።
በሚሳኤል ጥቃቱ 105 ሰዎች መቁሰላቸውንና የጥቁር ባህር መርከቦች ማዘዣ ጣቢያው ሙሉ በሙሉ መውደሙንም ነው የዩክሬን ልዩ ሃይል በቴሌግራም ገጹ ላይ ያሰፈረው።
ሬውተርስ የዩክሬን ልዩ ሃይል የማቾቹን ቁጥር እንዴት ማወቅ እንደቻለ ግልጽ አይደለም ብሏል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ ተገድለዋል ስለተባሉት ሰዎች ማንነትም ሆነ ቁጥር መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል።
ሞስኮ ባለፈው ሳምንት ከተፈጸመው ጥቃት በኋላ አንድ ሰው ስለመጥፋቱ ከመግለጽ ውጭ ዝርዝር ማብራሪያን አልሰጠችም።
በሴቫስታፖል የሚገኘው የሩሲያ አስተዳደር ኬቭ ተጨማሪ የሚሳኤል ጥቃት እንዳታደርስ የመከላከል ስራውን ማጠናከሩን አስታውቋል።
የሩሲያ አየር መቃወሚያ ቤልቤክ በተባለ አካባቢ የዩክሬን ሚሳኤሎችን መትቶ መጣሉንም ነው የሴቫስታፖል አስተዳዳሪ ሚኬል ራዝቮዤቭ የተናገሩት።
በ2014 ወደ ሩሲያ የተጠቃለለችው ክሬሚያ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ለምትፈጽማቸው የአየር ጥቃቶች መነሻ በመሆን እያገለገለች ነው።
በዚህም ምክንያት ኬቭ በክሬሚያ ላይ የተጠናከረ የሚሳኤል እና ድሮን ጥቃት እየፈጸመች ትገኛለች።