አረብ ኤምሬትስ ከጸሃይ የሚመነጭ ሃይልን በመጠቀም ከአለም ስድስተኛ ደረጃን ያዘች
በታዳሽ ሃይል ልማት በስፋት እየሰራች ያለችው ኤምሬትስ የጸሃይ ሃይልን በመጠቀም ከአረቡ አለም ቀዳሚዋ ሆናለች
አውስትራሊያ፣ ኔዘርላንድስ እና ጃፓን እስከ 3ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል
አረብ ኤምሬትስ ከጸሃይ የሚመነጭ የኤሌክትሪክ ሃይልን በስፋት ከሚጠቀሙ የአለማችን ሀገራት መካከል ተመደበች።
ሀገሪቱ የሶላር ሃይልን በብዛት በመጠቀም ከአለም ስድስተኛ በአረቡ አለም ደግሞ ቀዳሚ ሆናለች።
በ2022 1 ሺህ 921 ኪሎዋት በስአት በመጠቀም ጀርመን እና አሜሪካን አስከትላ ስድስተኛ ደረጃን መያዟን የአለም የኢነርጂ የ2023 ስታስቲካዊ ጥናት አመላክቷል።
አለም የገንዘብ ተቋም መረጃ እንደሚያሳየው ከጸሃይ እና ንፋስ የሚገኘው ሃይል እያደገ መጥቶ በአሁኑ ወቅት ከጠቅላላ የሃይል ፍላፎት 17 በመቶውን መሸፈን ችሏል።
ይሁን እንጂ ከታዳሽ ምንጮች የሚገኘው ሃይል ከድንጋይ ከስል ከሚገኘው (77 በመቶ) በብዙ እጥፍ ያነሰ ነው።
በ2022 በመላው አለም ከጸሃይ ሃይል የተገኘው ሃይል 192 ጊጋዋት ሲሆን፥ በዚሁ አመት ከታዳሽ ምንጮች ከተገኘው ሃይል ሁለት ሶስተኛውን ይሸፍናል።
ከጸሃይ ሃይል የሚገኘው ሃይል በየአመቱ እየጨመረ እንዲሄድ እንደ ኤምሬትስ፣ አውስትራሊያ፣ ህንድ እና ብራዚል ያሉ ሀገራት የጀመሯቸው የሶላር ፕሮጀክቶች ትልቅ አበርክቶ አላቸው።
የአለማቀፉ የአቶሚክ ሃይል ተቋም የ2023 የታዳሽ ሃይል ሪፖርት በቀጣዮቹ ሁለት አመታት በበርካታ ሀገራት የሶላር ፓኔሎች ይገጣጠማሉ ብሏል።
ይህም በ2024 ከሶላር ፕሮጀክቶች የሚገኘውን የኤሌክትሪክ ሃይል 140 ጊጋዋት እንደሚያደርሰው (ከ2022 በ30 በመቶ የሚልቅ) ነው ያመላከተው።
አውስትራሊያ፣ ኔዘርላንድስ፣ ጃፓን እና እስራኤል ከዜጎቻቸው ቁጥር አንጻር የጸሃይ ሃይልን በስፋት በመጠቀም ከ1ኛ እስከ 4ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
በታዳሽ ሃይል ላይ በስፋት እየሰራች የምትገኘው አረብ ኤምሬትስም እንደ ጀርመን እና አሜሪካ ካሉ ሀገራት በበለጠ ከጸሃይ የሚገኝ ሃይልን በመጠቀም ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
5 ሺህ ሜጋዋት ያመነጫል ተብሎ የሚጠበቀው የሞሃመድ ቢን ረሺድ አል ማክቱም የሶላር ፓርክ ፕሮጀክትም የሀገሪቱ የታዳሽ ሃይል ልማት ማሳያ ተደርጎ ይነሳል።
ኤምሬትስ በ2030 ከጸሃይ የምታገኘውን የኤሌክትሪክ ሃይል አሁን ካለበት በሶስት እጥፍ ለማሳደግ አቅዳለች።