የሶማሊያ ጦር የአልሻባብን ከፍተኛ አመራር በቁጥጥር ስር አዋለ
አሊ መሀመድ አዳን የተባለው የሽብር ቡድኑ አባል በታችኛው ሸበሌ ግዛት የቡድን ሽብር አደጋዎችን በመምራት የሚታወቅ ነው
የሶማሊያ ጦር በአልሻባብ እጅ የነበሩ ግዛቶች መልሶ በመቆጣጠር ላይ ይገኛል
የሶማሊያ ብሔራዊ ጦር የአልሻባብን ከፍተኛ አመራር በቁጥጥር ስር አዋለ።
የአገሪቱ ብሔራዊ ጦር እንዳስታወቀው በደቡባዊ ሶማሊያ ባካሄደው ኦፕሬሸን የአልሻባብ ከፍተኛ አመራርን በቁጠጥር ሰር ማዋሉን ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል።
አሊ መሀመድ አዳን የተሰኘው ይህ የሽብር ቡድን አመራር በታችኛው ሸበሌ ግዛት የቡድን ሽብር አደጋዎችን በመምራት ክስ የሚፈለግ ሲሆን በትናንትናው ዕለት በጃናሊ ከተማ መያዙ ተገልጿል።
የሶማሊያ ጦር አልሻባብ ተቆጣጥሯቸው የነበሩ ቦታዎችን መልሶ በመቆጣጠር ላይ መሆኑን ገልጾ ለአገሪቱ መዲና ሞቃዲሾ ቀርቦ የነበረው አልሻባብ ቀስ በቀስ ወደ ገጠር ከተሞች እየተመለሰ በተቃራኒው ደግሞ የአገሪቱ ጦር ድል እየቀናው መሆኑን ዘገባው አክሏል።
አልሻባብ በሶማሊያ እስላማዊ መንግስት የመመስረት አላማ ይዞ መዋጋት ከጀመረ አስርት አመታትን ያሳለፈ ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ ብዙ አገራት በተናጥል እና በቡድን ጦር አዋጥተው ወደ ስፍራው ልከዋል።
የአፍረካ ህብረት የሶማሊያ ተልዕኮ ወይም አሚሶም ከፈረንጆቹ 2007 ዓመት ጀምሮ ከምስራቅ አፍሪካ አገራት የተውጣጣ ጦር የሶማሊያ ብሔራዊ ጦር አልሻባብን ለማጥፋት የጀመረውን ዘመቻ በመደገፍ ላይ ይገኛል።