የሶማሊያ ፕሬዝዳንት የእርሳቸውንና የመንግስታቸውን ስልጣን ለማራዘም የተላለፈውን ውሳኔ ውድቅ አደረጉ
ውሳኔውን ያሳለፈው የሃገሪቱ የታችኛው ምክር ቤት ለመጪው ቅዳሜ አስቸኳይ ስብሰባን ጠርቷልም ተብሏል
ፋርማጆ ውሳኔውን ውድቅ በማድረግ ወደ መስከረም 17ቱ ስምምነት እንደሚመለሱ አስታውቀዋል
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብድላሂ ሞሃመድ (ፋርማጆ) ስልጣናቸውን ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት ለማራዘም የተወሰነውን ውሳኔ ውድቅ አደረጉ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ውሳኔውን ትተው ባሳለፍነው መስከረም 17 ከተለያዩ የፖለቲካ ተዋናዮች ጋር በተደረሰው ስምምነት መሰረት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ምርጫ ለማድረግ ልክ ዝግጁ መሆናቸውን በማስታወቅ ሁሉም አካላት የሃገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ከሚያናጋ ድርጊት እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሃገሪቱን የጸጥታ አካል ፖለቲካዊ መልክ ማላበስ፣መከፋፈል እና ንብረት ማውደም እንዲቆምም ጥሪ አቅርበዋል ፋርማጆ፡፡
የመስከረም 17ቱ ስምምነት በፌዴራል መንግስቱ እና በ5ቱ የሃገሪቱ ክልላዊ መስተዳድር መሪዎች እንዲሁም በሞቃዲሾ ገዢ የተፈረመ ነበር፡፡
ፋርማጆ ይህን ያደረጉት ደጋፊዎቻቸው የነበሩ የክልል መንግስታት መሪዎች እና ባለስልጣናት ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ጭምር ስልጣን የማራዘሙን ውሳኔ በመቃወማቸው ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሃመድ ሮብል ጨምሮ የሂርሸበሌ እና የጋልሙዱግ ክልል ፕሬዝዳንቶች ውሳኔውን ውድቅ ማድረጋቸው ፋርማጆ ውጥናቸውን እንዲገቱ አስገድዷል፡፡
ደጋፊዎቻቸው የነበሩ ባለስልጣናት ጭምር እንዲህ ለመሆናቸው ምክንያቱ የከበደ የውጭ ሃገራት እና ግለሰቦች ተጽዕኖ ነው ሲሉ ነው ፋርማጆ የወቀሱት፡፡
የሃገሪቱ የታችኛው ምክር ቤት የፋርማጆንና የመንግስታቸውን ስልጣን ለተጨማሪ 2 ዓመታት ለማራዘም ወስኖ ነበር፡፡
ሆኖም ውሳኔው በሞቃዲሾ ግጭት እንዲቀሰቀስና ፕሬዝዳንቱን በሚደግፉ እና በማይደግፉ የሃገሪቱ ጦር አባላት መካከል አመጽ እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆኗል፡፡
በአመጹ በርካቶች ሞቃዲሾን ለቀው መሰደዳቸውም ነው የተነገረው፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት በሶማሊያ ላይ አንዣቧል፡፡
ይህነኑ ተከትሎ ትናንት በሃገሪቱ ቴሌቪዥን የተላለፈ ንግግርን ያደረጉት ፋርማጆ ከነገ በስቲያ ቅዳሜ በአስቸኳይ ከሚሰበሰበው ምክር ቤቱ ፊት እንደሚቀርቡና ምክር ቤቱ ውሳኔውን ውድቅ እንዲያደርግ እንደሚያግባቡ አስታውቀዋል፡፡
ምክር ቤቱ የፕሬዝዳንቱን ማግባቢያ የሚቀበለው ከሆነ በፊርማቸው አጽድቀው ህግ ያደረጉት ውሳኔ ውድቅ የሚደረግ ይሆናል፡፡
ይህ የፋርማጆ እርምጃ ውሳኔውን ሲተቹ በነበሩ ምዕራባዊ ኃያል ሃገራት ጭምር ተወድሷል፡፡