የሶማሊያ ጦር ፍርድ ቤት ከሽብር ጋር በተያያዘ ሁለተ የውጭ ሀገራት ዜጎች በእስር እንዲቀጡ ወሰነ
የእስር ቅጣት የተላፈባቸው ግለሰቦች የብሪታኒያና የማሌዥያ ዜግነት ያላቸው መሆኑ ታውቋል
ግለሰቦቹ ከአል ሸባብ የሽበር ቡድን ጋር አብረው ሲሰሩ ነበር በሚል ነው የቅጣት ውሳኔው የተላለፈባቸው
የሶማሊያ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት ነበራቸው ባላቸው ሁለት የውጭ ሀገር ዜጎች ላይ የእስር ቅጣት ማሳለፉ ተሰምቷል።
የብሪታኒያና የማሌዥያ ዜግነት ያላቸው ግለሰቦቹ ለአል ሸባብ የሽብር ቡድን የውጭ ሀገራት ዜጎችን እየመለመሉ ሲቀጥሩ ነበር በሚል ነው ጥፋተኛ ተብለው ወታደራዊ ፍርድ ቤት የቀረቡት።
በዚህም ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ናቸው ያላቸውን ግለሰቦች እያንዳንዳቸው በ15 ዓመት እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ማሳለፉን ሲ.ጂ.ቲ.ኤን አፍሪካ ዘግቧል።
የእስር ቅጣቱ የተወሰነባቸው ግለሰቦቹም አንቶኒ ባይረንስ የተባለ የብሪታኒያ ዜጋ እና ቡስታቂም ቢን አብዱልሀሚድ የተባለ የማሌዢያ ዜጋ ናቸው።
የ44 ዓመቱ በሪታኒያዊ አንቶኒ ባይረንስ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2010 ወደ ሞቃዲሾ ያቀና ሲሆን፤ ከበርካታ የአል ሸባብ የሽብር ቡድን አመራሮች ጋር በመገናኘት በሀገሪቱ የተለያዩ የሽብር ተግባራትን ሲፈጽም የነበረ ሲሆን፤ በፈረንሳይ የሽብር ጥቃት እንዲፈፀም አቅዶ እንደነበረም ተነግሯል።
የ34 ዓመቱ ማሌዥያዊ አብዱል ሀሚድ ደግሞ በአውሮፓውያኑ 2009 ወደ ሶማሊያ መግባቱ የተነገረ ሲሆን፤ ከሽበር ቡድኑ ጋር በመሆን የተለያዩ ተግባራት ላይ መሳተፉ ተነግሯል።
የእስር ቅጣት የተላለፈባቸው ሁለቱም ግለሰቦች በአውሮፓውያኑ በ2019 ወደ የመን ለማምለጥ ሲሞክሩ ፑንትላንድ አካባቢ በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ወታደራዊ ፍድር ቤቱ አስታውቋል።