የኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የወደብ የመግባቢያ ስምምነት “የሶማሊያን ሉዓላዊነት የሚጻረር ነው” ብሏል
የሶማሊያ መንግስት በኢትዮጵያ የሚገኙትን የሀገሪቱን አምበሳደር ለምክክር መጥራቱን አስታወቀ።
በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ መካከል በተደረሰው የወደብ የመግባቢያ ስምምነት ላይ አስቸኳይ ስብሰባ የተቀመጠው የሀገሪቱ ካቢኔ ውሳኔዎችን ማሳለፉን የሶማሊያ የዜና አገልግሎት (ሶና) ዘግቧል።
በዚህም የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ መንግስት በኢትዮጵያ የሚገኙትን የሀገሪቱን አምባሳደር አብዱላሂ መሀመድ ወርፋን ለምክክር ወደ ሞቃዲሾ መጥራቱን አስታውቋል።
- የኢትዮጵያን ቀይ ባህርን የመጠቀም ፍላጎት ያሳካል የተባለ የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙን መንግስት ገለጸ
- ኢትዮጵያ ወደብ እንድትከራይ እና በምላሹ ለሶማሊላንድ እውቅና እንድትሰጥ ስምምነት ላይ መደረሱን ሶማሊላንድ አስታወቀች
በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ መካከል በተደረሰው የወደብ ግንኙነት የመግባቢያ ስምምነት የሶማሊያ ግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት የሚጻረር መሆኑንም ካቢኔው አስታውቋል።
የሶማሊያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው አስቸኳይ ስብሰባው፤ “የኢትዮጵያ መንግስት በውስጥ ጉዳያችን ላይ እያደረገ ያለው ጣልቃ ገብነት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት እና አለም አቀፍ ህጎችን የሚጥስ ነው” ብሏል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ ሁሉም አለም አቀፍ ድርጅቶች በጉዳዩ ላይ ጣልቃ እንዲገቡ ጥሪ አቅርቧል።
ካቢኔው ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የደረሰችውን የመግባቢያ ስምምነት ውድቅ ያደረገ ሲሆን፤ “ስምምነቱ ባዶና እና ህጋዊ መሰረት የሌለው ነው” ብሏል።
የሶማሊያ መንግስት በጉዳዩ ላይ በሰጠው መግለጫ የኢትዮጵያ እርምጃ የሶማሊያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የሚጥስ “ግልጽ ጥቃት ነው” ብሏል።
የሶማሊያ መንግስት ቃል አቀባይ ፋርሃን ጂማሌ "የኢትዮጵያ ድርጊት መልካም ጉርብትናን እንዲሁም የቀጠናውን ሰላምና መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥል ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን የመጠቀም ፍላጎቷን ለማሳካት መንገድ የሚጠርግ እና የወደብ አማራጮችን የሚያሰፋ የመግባቢያ ሰነድ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ላይ ትናንት መፈራረሟ ይታወቃል።
ስምምነቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የሶማሌ ላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ በትናንትናው እለት ተፈራርመዋል።
በኢትዮጵያና እና የሶማሊላንድ መካከል የተፈረመው ስምምነት ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ በሊዝ ወታደራዊ ካምፕ እንድታገኝ እና የባህር ላይ የንግድ እንቅስቃሴ እንድታደርግ መንገድ የሚከፍት መሆኑን የጠ/ሚኒስትሩ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተናግረዋል።
በምላሹ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ እንደምትወስድ የገለጹት አምባሳደር ሬድዋን ተጨማሪ ዝርዝር ግን አልሰጡም።
የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ ኢትዮጵያ ለባህር ኃይሏ የሚሆን ወደብ እንድትከራይ እና በምትኩ ለራስ ገዟ ሶማሊላንድ ይፋዊ እውቅና እንድሰጥ ሰምምነት ላይ ተደርሷል ብሏል።
የሶማሌ ላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ "ኢትዮጵያ 20 ኪሎሜትር የሚረዝም የባህር ጠረፍ ለ50 ዓመታት በሊዝ እንድትከራይ እና በምትኩ ለሶማሊላንድ ይፋዊ እውቅና እንድትሰጥ ተስማምተናል" ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጠቅሷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከወራት በፊት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የባህር በር ለመጠቀም እንደምትደራደር መናገራቸው ይታወሳል።
ይሁን እንጅ ሶማሊያ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይን ጥሪ አልተቀበለችም ነበር።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በውቅቱ ባወጣው መግለጫ "የሶማሊያ ሉአላዊነት እና የግዛት አንድነት- መሬት፣ ባህር እና አየር- ቅዱስ እና ለድርድር የማይቀርቡ ናቸው" ሲል ማሳሰቡ ይታወሳል።