ስለራስገዟ ሶማሊላንድ እስካሁን የምናውቀው
ሶማሊላንድ በፈረንጆቹ 1991 ከሶማሊያ መነጠሏን ብታውጅም አለማቀፉ ማህበረሰብ እንደሀገር እውቅና አልሰጣትም
መዲናዋን ሃርጌሳ ያደረገችው ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የደረሰችው ስምምነት ምን ያስገኝላታል?
ሶማሊላንድ የሶማሌው ወታደራዊ መሪ ዚያድ ባሬ ከስልጣን በተወገደ ማግስት ከሶማሊያ ተነጥላ ነጻ ሀገር መሆኗን አውጃለች።
ዚያድ ባሬ ኢሳቅ በተሰኘው የሶማሊላንድ ጎሳ አባላት ላይ የተከተለው ፖሊሲ ለውድቀቱ አንዱ ምክንያት ተደርጎ ይነሳል።
ከ1987 እስከ 1989 ባሉት ሶስት አመታት ብቻም ከ100 ሺህ በላይ የኢሳቅ ጎሳ አባላት መገደላቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።
ሶማሊላንድ ሲያድ ባሬ እንደተወገደ በ1991 ከሶማሊያ መገንጠሏን ብታውጅም ሞቃዲሾም ሆነ ሌሎች ሀገራት እንደነጻ ሀገር እውቅና አልሰጧትም።
አለማቀፉ ማህበረሰብ እውቅና ባይሰጣትም ሉአላዊ ሀገራት የሚያሰኙ ተግባራትን መፈጸም ከጀመረች ሶስት አስርት ተቆጥረዋል።
ራስ ገዝ ግዛቷ ከ1996 ጀምሮ የሶማሊላንድ ፓስፖርት አስተዋውቃለች፤ ህገመንግስት አጽድቃ፣ ምክርቤቶች አዋቅራም በየአመስት አመቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እያካሄደች ነው (ነጻነቷን ካወጀች ጀምሮ ሶስት ምርጫዎችን አድርጋለች)።
ከሀገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመመስረት ጥረት እንደምታደርግም ትገልጻለች። በአሜሪካ፣ ብሪታንያ፣ አረብ ኤምሬትስ እና ታይዋን ጉዳይ ማስፈጸሚያ ቢሮዎች እንዳሏትም ታነሳለች።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ከበርካታ ሀገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊና የልማት ትብብር አለኝ፤ የራሴን የጸጥታ ሃይል አደራጅቼ (የባህር ሃይል ጭምር) ሰላምና ደህንነቴን እያረጋገጥኩ እገኛለሁ በሚልም የሀገርነት እውቅና እንዲሰጣት ስትወተውት ይደመጣል።
የሶማሊያ መንግስት ግን እንግሊዝ በሞግዚትነት ያስተዳደረቻት ሶማሊላንድ “ከእናት ሀገሯ ሶማሊያ አልተነጠለችም፤ የግዛቴ አካል ናት” በሚለው አቋሙ እንደጸና ነው።
የሶማሊላንድ እውነታዎች
መዲና - ሃርጌሳ
ስፋት - 177 ሺህ ስኩዌር ኪሎሜትር
የህዝብ ብዛት - 5 ነጥብ 7 ሚሊየን
ቋንቋ - ሶማሊ፣ አረብኛ፣ እንግሊዝኛ
መሪ
ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ
ሙሴ ቢሂ አብዲ በህዳር ወር 2017 በተካሄደ ምርጫ አሸንፈው አህመድ ሲላንዮን ተክተዋል።
ቢሂ የገዥው ኩልሚየ ፓርቲ መስራችና መሪው ሲላንዮ በ2010ሩ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ካሸነፉ በኋላ የፓርቲው ሊቀመንበር ሆነው አገልግለዋል።
የቀድሞው የአየር ሃይል አብራሪ በ1990ዎቹ የሶማሊላንድ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ማገልገላቸው ይታወሳል።
የፕሬዝዳንት ቢሂ የስልጣን ዘመን በህዳር ወር 2022 ይጠናቀቅ የነበረ ሲሆን የሶማሊላንድ የምርጫ ኮሚሽን የፋይናንስና ቴክኒካዊ ጉዳዮችን እንደምክንያት በመጥቀስ ምርጫውን ለሁለት አመት አራዝሞታል።
ተቃዋሚ ፓርቲዎች የምርጫውን መራዘም የተቃወሙ ሲሆን፥ ሶማሊላንድ ለአለም ከምትነግረው የዴሞክራሲያዊ ስርአት ገንብቻለሁና የሀገርነት እውቅና ስጡኝ ቅስቀሳ ይቃረናል በሚል እየተቹት ነው።
ከቅኝ ግዛት እስከ ነጻ ሀገር ምስረታ
1888 - ብሪታንያ ከወቅቱ የሶማሊላንድ መሪዎች (ሱልጣኖች) ጋር ስምምነት ደርሻለሁ በማለት አካባቢውን የቅኝ ግዛቷ አካል አድርጋ አወጀች
1899 - ሞሀመድ አብዱላህ የሃይማኖት አባት በብሪታንያ አገዛዝ ላይ አምጸው ደርቪሽ የተባለ ግዛት መስርተው ተዋጉ፤ በ1920 ተሸነፉ
1960 - ብሪቲሽ ሶማሊላንድ (የአሁኗ ሶማሊላንድ) እና የጣሊያን ሶማሊላንድ (የአሁኗ ሶማሊያ) ነጻነታቸው ታውጆና ተዋህደው የሶማሊያ ሪፐብሊክን ፈጠሩ
1991 - የቀድሞዋ የብሪቲሽ ሶማሊላንድ ከሶማሊያ ሪፐብሊክ ተነጥላ ነጻ ሀገር መሆኗን አወጀች
2001 – 97 በመቶ ህዝቧ የሶማሊላንድ ህገመንግስትን አጸደቀ፤
2016 - ሶማሊላንድ ከሶማሊያ የተነጠለችበትንና ነጻነቷን ያወጀችበት 25ኛ አመት ተከበረ፤ ይሁን እንጂ ለራስ ገዟ ግዛት እውቅና የሰጣት የለም
ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ከተላቀቀች በኋላ የቅኝ ግዛት ድንበሯን አስጠብቃ መቆየቷን የምትገልጸው ሶማሊላንድ እንደሀገር የሚያስቆጥሩ ነገሮችን ሁሉ አሟልቻለሁ ትላለች፤ ሀገራት እውቅና እንዲሰጧትም ብርቱ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች።
በትናንትናው እለት ከኢትዮጵያ ጋር የደረሰችው ስምምነት የሩብ ክፍለዘመን ጥረቷ ፍሬ ማፍራት መጀመሩን ያሳያል ተብሏል።
ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ በሊዝ ወደብና የጦር ሰፈር ስታከራይ ከኢትዮጵያ በምትኩ የሀገርነት እውቅናን እንደምታገኝ መገለጹ ይታወሳል።