ሶማሊያ ‘ከመንግስትዎ ጋር መክረው ይመለሱ’ ያለቻቸውን የኬንያ አምባሳደር አባረረች
ኬንያ በውስጥ ጉዳዮቼ ጣልቃ እየገባች ነው ስትል የከሰሰችው ሶማሊያ ከቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ ናይሮቢ በክልል ፕሬዝዳንቶች ላይ ሳይቀር ጫና ታደርጋለች ስትል ነው የገለጸችው
ሞቃዲሾ ናይሮቢ የሚገኙ አምባሳደሯንም ጠርታለች
ሶማሊያ የኬንያ አምባሳደርን አባረረች
በሶማሊያ የኬንያ አምባሳደር ተባረሩ፡፡
አምባሳደሩ ‘ከመንግስትዎ ጋር መክረው ይመለሱ’ በሚል የተባረሩት “ኬንያ በውስጥ ጉዳዮቼ ጣልቃ እየገባች ነው”ሲል በወቀሰው የፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆ መንግስት ሲሆን ናይሮቢ የሚገኙት የሶማሊያ አምባሳደርም ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ታዘዋል፡፡
የኬንያ መንግስት በሶማሊያ ሉዓላዊነት፣ግዛታዊ አንድነትና ፖለቲካዊ ነጻነት ላይ ጣልቃ እየገባ ነው ሲል መግለጫ ያወጣው የፋርማጆ መንግስት በድርጊቱ ማዘኑን ገልጿል፡፡
“ጣልቃ ገብነቱ የሃገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ከማናጋት ባለፈ ቀጣናዊ ችግር ሊፈጥር የሚችል ነው”ም ነው ያለው በውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር በኩል ባወጣው መግለጫ፡፡
መግለጫው “የኡሁሩ ኬንያ መንግስት ፖለቲካዊ ፍላጎቱን ለማስፈጸም በጁባ ላንድ ክልል ፕሬዝዳንት አህመድ መሃመድ ኢስላን (ማዶቤ) ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ይገኛል” ሲል የሚያትት ሲሆን ባሳለፍነው ወርሃ መስከረም ስምምነት ላይ ከተደረሰበት ሃገር አቀፍ ምርጫ አፈጻጸም ጋር እንደሚያያዝ አስታውቋል፡፡
በዚህ ምክንያት ናይሮቢ የሚገኙት አምባሳደር መሃመድ አህመድ ኑር ታርሳን ወደ ሃገር ቤት እንዲመለሱ እና ሞቃዲሾ የሚገኙት አምባሳደር ሉካስ ቱምቦ ወደ ናይሮቢ ተመልሰው ከመንግስታቸው ጋር እንዲመክሩ ታዘዋል፡፡
የሶማሊያን ድርጊት ያልተገባ ያለችው ኬንያ በበኩሏ ለእርምጃው ተመጣጣኝ ምላሽ እንደምትሰጥ በውጭ ጉዳይ ዋና ጸሃፊዋ አምባሳደር ማቻሪያ ካማው በኩል አስታውቃለች፡፡
ማቻሪያ ተጨማሪ ነገሮችን ከመናገር መቆጠባቸውንም ነው ጎብጆግ ኒውስ የዘገበው፡፡