ጠ/ሚ ዐቢይ “ኢትዮጵያ ከሶማሊያ መንግስትና ህዝብ ጋር የመጠላት ፍላጎት የላትም” አሉ
ጠ/ሚ ዐቢይ “የቀይ ባህርን የመጠቀም ጥያቄያችን ህጋዊ መሆኑን ለዓለም አሳይተናል” ብለዋል
“ኢትዮጵያ የምትከተለው ያፈረና የተደበቀ ዲፕሎማሲ አሁን መልክ እየቀየረ ነው” ሲሉ ገልጸዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ “ኢትዮጵያ ከሶማሊያ መንግስት እና ህዝብ ጋር ለመጠላት ፈጽሞ ፍላጎት የላትም” ሲሉ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ “ስብራትን መጠገን፤ ለትውልድ መታመን” በሚል ለብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በሰጡት ገለጻ ላይ ሰሞንኛውን የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ጉዳይ አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በጉዳዩ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፤ “ሶማሊያ ከማንም በላይ የኢትዮጵያ ወንድም፣ ዘመድ ጎረቤት ነች” ብለዋል።
“ባለፉት 10 ዓመታት በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሀገሪቱን ሰላም ለማስከበር የህይወት ዋጋ ከፍለዋል” ያሉ ሲሆን፤ “ለሶማሊያ ሰላም ኢትዮጵያ የከፈለችውን ዋጋ ማንም በዓለም ላይ የሚገን ሀገር የከፈለ የለም” ሲሉም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊያ መንግስት እና ህዝብ ጋር የመጠላት ፈጽሞ ፍላጎት እንደሌላትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስታውቀዋል።
“የኢትዮጵያ መንግስት በሶማሊያ አንድነት ላይ የሚታማ አይደልም” ያሉ ሲሆን፤ “አሁን ያለው የኢትዮጵያ መንግስት ለመጀመሪያ ጊዜ ሶማሊያውያን አንድ እንዲሆኑ በንግግር ሳይሆን በተግባር የሰራ መሆኑን ለአብንት አንስተዋል።
“የቀይ ባህርን የመጠቀም ጥያቄያችን ህጋዊ መሆኑን ለዓለም አሳይተናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ፤ “የእኛ ፍላጎት ቀይ ባህርን በመጠቀም ብቻ ነው” ሲሉም አብራርተዋል።
“ዓለም በሙሉ ይገባችዋልል እኮ ግን ነው የሚለው፤ ከኢትዮጵያ ለሚወሰድ ነገር ችግር የለውም፤ ለኢትዮጵያ መስጠት ሲሆን ነው ነውሩ” ብለዋል በንግግራቸው።
“የምንከተለው ዲፕሎማሲ ያፈረ እና የተደበቀ ዲፕሎማሲ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “አሁን መልክ እየቀየረ ነው፤ ይህ አጀንዳ አየር ላይ ከወጣ በኋላ አሁንም ብስለት እና ጥበብ በተሞላበት መንገድ መምራት ይፈልጋል” ብለዋል።
“በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መንግስታት መካከል ችግር ይፈጠራል ብዬ ስለማላስብ፤ በህዝቦች መካከል ጥላቻና ቁርሾ እንዳይፈጠር በሰለጠነ እና በተረጋጋ መንገድ መምራት ይፈልጋል” ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሄ አብዲ ከሳምንታት በፊት በአዲስ አበባ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል።
ስምምነቱን ተከትሎም ሶማሊላንድ የግዛቴ አንድ አካል ናት የምትላት ሶማሊያ የዲፕሎማሲ የበላይነት ለማግኘት የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ትገኛለች።
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ማህሙድ ከሰሞኑ ከአልጄዚራ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ጉዳዩን ሁላችንንም ተጠቃሚ በሚያደርግ መንገድ መፍታት ይቻላል ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል።
"ኢትዮጵያ ወደብ ቢኖራት ተቃውሞ የለንም፣ ለድርድርም ዝግጁ ነን ነገር ግን የሌላ ሀገር ግዛትን በመውሰድ ግን ሊሆን አይገባም" ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።