የአካባቢው አስተዳዳሪዎች ከጥቃቱ ጀርባ የአልሸባብ ታጣቂዎች አሉበት ብለዋል
በሶማሊያ በደረሰ ጥቃት 6 ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የሰባት ሰዎች ህይወት ማለፉን የአካባቢው ባለስልጣንት አስታውቀዋል።
ጥቃቱ በደቡባዊ ሶማሊያ ጌዶ ክልል ባሌድ ሀዎ በተባለች አነስተኛ ከተማ ውስጥ ሌሊት ላይ መፈጸሙን የአካባቢው ባለስልጣናት ለቪኦኤ ሶማልኛ ተናግረዋል።
የባሌድ ሀዎ አካባቢ ኮሚሽነር አብዲራሺድ አብዲ አሮግ እንደተናገሩት፤ ታጣቂዎች በአንድ ግቢ ላይ በከፈቱት ጥቃት አምስት ወንዶች እና ሁለት ሴቶች በድምሩ ሰባት ሰዎች ተገድለዋል ብለዋል።
አሮግ “ትናንት ሌሊት 9 ሰዓት ላይ ከፍተኛ የሆነ የተኩስ ድምጽ ሰማን፤ ይህ የሆነው የጥበቃ ፓትሮሎች ፈረቃ በሚለዋወጡበት ሰዓት ነው፤ ገዳዮቹ ይህንን እንደ መላክም አጋጣሚ ተጠቅመው ነው ጥቃቱን የፈጸሙት” ብለዋል።
“ወታደሮች ፈጣን ምላሽ በመስጠት በስፍራው ላይ ሲደርሱ የሞቱ ሲቪል ሰዎችን እንደተመለከቱ እና ከሞቱት መካለም ህጻት፣ ሴቶች እና ወንዶች እንደሚገኙበት” እዲሁም የተወሰኑት ደግሞ እንደቆሰሉ ተናግረዋል።
“ከሞቱት ሰዎች መካከልም በብሄር ኦሮሞ የሆኑ 6 ኢትዮጵያውን መሆናቸውን እና አንዲት ሴት ሶማሊያዊት እንደምትገኝበት” አሮግ ገልጸዋል።
ሶማሊዊቷ ሴት የኢትዮጵያውያኑ ጎረቤት ስትሆን፤ ህይወቷ ሊያልፍ የቻለው የተኩስ ድምጽ በመስማት ከቤቷ ስትወጣ እንደሆነም ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።
በጥቃቱ የተጎዱ ሰዎችን ወደ ህክምና ማእከላት መወሰዳቸውን የገለጹት አሮግ፤ ከቆሰሉት ሰዎች መካከል የተወሰኑት ለህክምና ወደ ኬንያ መንዴራ መወሰዳቸውንም ተናግረዋል።
“የጥቃት ፈጻሚዎቹን ዱካ አለን፤ ጉዳዩንም እየመረምርን ነው፤ ነገር ግን ሰዎችን የሚገድሉ አሸባሪዎች አሉን” ያሉት አሮግ፤ “አሸባሪዎቹ ሰዎችን የሚገድሉ ናቸው፤ በዚህ ግድያም እነሱን ነው ተጠያቂ የምናደርገው” ብለዋል።
አሮግ በሌድ ሀዎ የድንበር ከተማ ነች፣ ከኬንያ እና ከኢትዮጵያ የሚመጡ ሰዎች እንዲሁም ከሶማሊያውያኖች እንቅስቃሴ ብፋት የሚታይበት ስፍራ ነች ያሉ ሲሆን፤ ጥቃት አድራሾቹ ያለምንም ልዩነት መተኮሳቸውን ተናግረዋል።
የጁባ ላንድ የደህንነት ሚኒስቴር የሱፍ ሁሴን ዳሙል በበኩላቸው፤ አስተዳራቸው ጥቃቱን አልሸባብ በከተማዋ በንግድ እና በሌሎች ስራ ላይ ተሰማርተው በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ አነጣጥሮ የተፈጸመ መሆኑን ያምናል ብለዋል።
ጥቃቱን አራት ሰዎች መፈጸማቸውን እና የጸጥታ አካላት ስርም በሞተር ሳይክል አምልጠው አልሸባብ ወደሚቆጣጠረው ጋን ዳዌ አካባቢ መግባታቸውንም ተናግረዋል።
ስለ ጥቃቱ መንስኤ የተጠየቁት ሚኒስትሩ፤ ታጣቂዎቹ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያውያን መካከል “ግጭት ለመፍጠር” አስበው ያደረጉት ይሆናል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
"ጥቃት ፈጻዎች ሁለት አላማዎች አሏቸው ያሉት ሚኒስትሩ፤ አንደኛው በእነሱ ዘንድ የሚታወቀው ሽብርተኝነት ነው፤ ሁለተኛው ከእኛ ጋር የሚኖሩ እና የሚሰሩትን ሰዎች ለማተራመስ እና እንዲሸሹ ለማስገደድ ነው" ብለዋል
የሶማሊያ ባለስልጣናት ለጥቃቱ አል ሸባብን ተጠያቂ ቢያደርጉም አልሸባብ እስካሁን ስለ ጥቃቱ አስተያየት አልሰጠም።