ሶማሊያና ኬንያ የአውሮፕላኑን መከስከስ ምክንያት በጋራ ለመመርመር ተስማሙ
የተከሰከሰው አውሮፕላን የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያገለግሉ የእርዳታ ቁሳቁሶችን ይዞ ነበር
የኬንያና የሶማያ ፕሬዚዳንቶች የአውሮፕላኑን መከስከስ ጉዳይ በጋራ ለመመርመር ተስማሙ
የኬንያና የሶማያ ፕሬዚዳንቶች የአውሮፕላኑን መከስከስ ጉዳይ በጋራ ለመመርመር ተስማሙ
የሶማያው ፕሬዚዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ በሀገራቸው አየር ክልል በትናንትናው እለት ተመቶ የወደቀውን አውሮፕላን መነሻ ምክንያት ለማወቅ ከጎረቤታቸው ኬንያ ጋር በጋራ ሊያጣሩ መስማማታቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ የኬንያው አቻቸው ኡሁሩ ኬንያታም በጉዳዩ ዙሪያ የሀገራቸው ሲቪል አቪየሽን ተቋም ከሶማሊያ አቻው ጋር በጋራ እንዲሰራ ፈቃደኛ ሆነዋል፡፡
በወደቀው አውሮፕላን ስድስት ሰዎች ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን ሁለቱ ኬንያውያን ፣ አራቱ ደግሞ ሶማሊያውያን ናቸው ተብሏል፡፡ይህን ተከትሎም ኬንያ በሶማሊያ ባርዳሌ አካባቢ የወደቀው አውሮፕላን መነሻ ምክንያት እንዲታወቅ መጠየቋን የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ያወጣው መግለጫ ያመለክታል፡፡
አውሮፕላኑ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያገለግሉ የእርዳታ ቁሳቁሶችን ይዞ ነበር ተብሏል፡፡ኡሁሩ ኬንያታ የሶማሊያው አቻቸው ሙሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ጉዳዩን በጋራ ለማጣራት ላቀረቡት ጥያቄ አወንታዊ ምላሽ ከመስጠትም ባለፈ ምስጋናም አቅርበዋል ነው የተባለው፡፡
የሶማሊያው ፕሬዚዳንት አብዱላሂ ፋርማጆም የሀገራቸው ሲቪል አቪዬሽን መስሪያ ቤት አውሮፕላኑ የወደቀበትን መነሻ ምክንያት እንዲያጣራ ማዘዛቸውን ለአሁሩ ኬንያታ በስልክ ነግረዋቸዋል፡፡
በዚህም መሰረት ኡሁሩ ኬንያ የሀገራቸው ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ከሶማሊያ አቻው ጋር ሆኖ አውሮፕላኑ የወደቀበትን ምክንያት እንዲጣራ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡
በአውሮፕላኑ ውስጥ አብራሪው ፣ረዳት አብራሪው፣የበረራ መሐንዲስ፣ሰልጣኝ አብራሪ፣ እና ሁለት የበረራ ሰራተኞች ነበሩ፡፡አውሮፕላኑ ተመቶ የወደቀው በደቡባዊ የባርዳአሌ ከተማ ለማረፍ በተዘጋጀበት ጊዜ እንደነበር ተሰምቷል፡፡የወደቀው አውሮፕላን 5Y-AXO ተሰኘ ሲሆን በኬንያ የተመዘገበ የአፍሪካን ኤክስፕረስ አየር መንገድ አውሮፕላን ነው፡፡