ያሰበችውን ምርጫ በያዘችው እቅድ መሰረት እንደምታካሂድ ሶማሊያ ገለጸች
የሃገሪቱ የደህንነት ሹም ከሃላፊነት መነሳታቸውን ተከትሎ በጠ/ሚ ሮብል እና በፕሬዝዳንት ፋርማጆ መካከል ቅራኔ መፈጠሩ የሚታወስ ነው
ትናንት እሁድ ከተመድ ምክትል ዋና ጸሃፊ አሚና መሃመድ ጋር የተወያዩት የሶማሊያ ጠ/ሚ መሃመድ ሮብል ይህንኑ ገልጸዋል
የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር መሃመድ ሁሴን ሮብል ሃገራቸው ቀደም ሲል በያዘችው እቅድ መሰረት ምርጫ እንደምታካሂድ ገለጹ፡፡
ሮብል ይህን ያሉት ከተመድ ምክትል ዋና ጸሃፊ አሚና መሃመድ ጋር በተወያዩበት በትናንትናው ዕለት ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰሞኑ የሃገሪቱን የደህንነት ሹም ኮሎኔል ያሲን አብዱላሂ ማህሙድ ከሃላፊነት አንስተዋል፡፡
በፋርማጆ የተሾሙት እና ከፕሬዝዳንቱ የቀረበ ግንኙነት እንዳላቸው የተነገረላቸው የደህንነት ሹሙ የሳይበር ደህንነት አባል ከነበረችው ኢክራን ታህሊል ፋራህ መጥፋት ምናልባትም ግድያ ጋር በተያያዘ ነው ከሃላፊነት የተነሱት፡፡
በምትካቸውም አብዱላሂ መሃመድ ኑር የሽግግር ጊዜውን የምመራው እኔ ነኝ በሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሮብል ተሾመዋል፡፡
ይህን ተከትሎ እርምጃው አግባብ አይደለም ካሉት ከፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ (ፋርማጆ) ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብተዋል፡፡
ፋርማጆ በበኩላቸው ኮሎኔል ያሲን አብዱላሂ ማህሙድን የደህንነት አማካሪያቸው አድርገው ሾመዋል፡፡
ቅራኔው ከመጪው ጥቅምት መባቻ ጀምሮ እስከ ወርሃ ህዳር የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ምርጫውን ለማካሄድ የተያዘውን እቅድ እንዳያስተጓጉለው ተስግቷል፡፡
ከከፍተኛ የተመድ ዲፕሎማቷ አሚና ጋር የተወያዩት ሮብል ግን ምርጫው በተያዘለት እቅድ መሰረት እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ፋርማጆም ቢሆኑ ምርጫውን በወቅቱ በሰላማዊ መንገድ ለማካሄድ ያላቸውን ቁርጠኝነት ለምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡
ፋርማጆ የሴቶችን ተሳትፎ ለመጠበቅም ነው ቃል የገቡት፡፡
አሚና በበኩላቸው የሴቶች የ30 በመቶ የፓርላማ ውክልና እንዲጠበቅ ጠይቀዋል፡፡
ናይሮቢ የሚገኘውን የድርጅታቸውን የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ማስተባበሪያ ቢሮን የጎበኙት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ከኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና ከታንዛኒያዋ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ስሉህ ጋር ተወያይተዋል፡፡