ሶማሊያ በዘንድሮው ሃጅ መዘጋት እስከ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ታጣለች
የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ እስከ አንድ ቢሊዬን ዶላር ያጣል
የዘንድሮው የሃጅ የጉዞ ስነ ስርዓት መቋረጡ ሶማሊያን 5 መቶ ሚሊዮን ዶላር እንደሚያሳጣት ኳርትዝ አፍሪካ የተሰኘ የዜና አውታር ዘገበ፡፡
ሞቃዲሾ ይህን የምታጣው በታላቁ ሃይማኖታዊ ስነ ስርዓት ላይ ታቀርብ የነበረው የእርድ እንስሳት ቁጥር በእጅጉ በመቀነሱ ምክንያት ነው፡፡
ይህም ግመልን የመሳሰሉ የቁም እንስሳትን በመላክ ከወጪ ንግዱ ታገኝ የነበረውን ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ገደማ ገንዘብ ያሳጣታል፡፡
የእርድ እንስሳት የወጪ ንግድ ምጣኔዋ ከግማሽ በላይ እንደሚያሽቆለቁልም የቅርብ ጊዜ የዓለም ባንክ ጥናት ያመለክታል፡፡
ራስ ገዟ ሶማሊ ላንድም ብትሆን ቀላል የማይባል የውጭ ምንዛሬን ታጣለች እንደ ዘገባው ከሆነ፡፡ ከ250 ሚሊዮን ዶላር እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ዋጋ ያለው የእርድ እንሰሳት የወጪ ንግድ ግብይት ከሃርጌሳ በየዓመቱ ይፈጸማልም፡፡
በጥቅሉ ከአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የአንድ ቢሊዬን ዶላር ያለው የቁም እንስሳት የወጪ ግብይት እንደሚፈጸምም ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት፡፡
ሳዑዲ በየዓመቱ ሃጅ በመጣ ቁጥር እስከ 3 ሚሊዬን የሚደርሱ የእርድ እንስሳትን ወደ ሃገሯ እንደምታስገባም ከዓመት በፊት የወጣ አንድ ጥናት ይጠቁማል፡፡
ወደ ህዝበ ሙስሊሙ ቅዱስ ከተማ መካ በሚደረገው ዓመታዊ ጉዞ እስከ 2 ሚሊዬን የሚደርሱ የእምነቱ ተከታዮች ይሳተፉ ነበር፡፡
ሆኖም የዘንድሮው ሃጅ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ከአስር ሺ በማይበልጡ ምዕመናን እንደሚከበር የሳዑዲ ባለስልጣናት ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው፡፡