ሶማሊላንድ 4ኛ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫዋን በሰላም አጠናቃ የድምጽ ቆጠራ ጀመረች
የወቅቱን ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲን ጨምሮ ሶስት እጩዎች የተሳተፉበት ምርጫ ውጤት በቀጣዩ ሳምንት ይፋ ይደረጋል ተብሏል
ተፎካካሪዎቹ የሶማሊላንድን የ33 አመታት የነጻ ሀገርነት እውቅና ጥያቄ ለመመለስ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል
ራስ ገዟ ሶማሊላንድ በትናንትናው እለት ያካሄደችው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በሰላም መጠናቀቁን አስታወቀች።
ከ1 ሚሊየን በላይ ሰዎች በ2 ሺህ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ድምጻቸውን ሰጥተው ከምሽት ጀምሮ ቆጠራ መጀመሩን የሶማሊላንድ ምርጫ ኮሚሽን ገልጿል።
የፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ውጤት ህዳር 12 2017 በይፋ እንደሚገለጽም ነው የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሙሴ ሃሰን ዩሱፍ የተናገሩት።
የሶማሊላንድ ፖሊስ ሃይል ዋና አዛዥ ጀነራል ሞሀመድ አዳን ሳቃድሂ “ምርጫው ዴሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ ሆኖ ተጠናቋል፤ አንድም ችግር ሪፖርት አልተደረገም” ማለታቸውን ቪኦኤ አስነብቧል።
በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው የወቅቱ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲን ጨምሮ ሶስት እጩዎች ተሳትፈዋል። ሶስቱም ተፎካካሪዎች በምርጫ ቅስቀሳቸው የራስ ገዟን ኢኮኖሚ ማሳደግና ዴሞክራሲያዊ ስርአትን ማጎልበት ላይ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል። የሶማሊላንድ የ33 አመታት ያልተመለሰ የነጻ ሀገርነት አለማቀፍ እውቅና ምላሽ ማስጠትም ቁልፍ አጀንዳቸው አድርገውታል።
ገዥውን የሰላም፣ አንድነት እና ልማት ፓርቲ (ኩልሚየ) የወከሉት ሙሴ ቢሂ አብዲ ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን ከዋዳኒ ፓርቲው አብዲራህማን ሞሀመድ አብዱላሂ እና ከፍትህና ልማት ፓርቲው ፈይሰል አሊ ዋራቢ ጋር ተፎካክረዋል።
ሶማሊላንድ ከዚያድ ባሬ አስተዳደር መሸነፍ (1991) በኋላ ነጻ ሀገርነቷን ካወጀች በኋላ የትናንቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አራተኛው ነው።
ራስ ገዟ ሶማሊላንድ ምርጫ ብታካሂድም፤ የራሷን መገበያያ ገንዘብ ብትጠቀምም፤ ወታደራዊ እና የጸጥታ ሃይል ብታደራጅም፤ ፓስፖርት ብትሰጥም አንድም ሀገር እስካሁን ለነጻነቷ እውቅና አልሰጠም።
ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመችው የወደብ ኪራይ ስምምነት አዲስ አበባን ለሃርጌሳ እውቅና ያሰጣል ቢባልም ከኢትዮጵያ በኩል እስካሁን በይፋ የተነገረ ነገር የለም።
ሶማሊያ በበኩሏ የግዛቴ አካል ናት ከምትላት ሶማሊላንድ ጋር ኢትዮጵያ የደረሰችው ስምምነት ሉአላዊነቴን ይጋፋል በሚል የመግባቢያ ስምምነቱ እንዲሰረዝ መጠየቋ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ አምባሳደርን ከማባረር አንስቶ በሶማሊላንድ እና ፑንትላንድ የሚገኙትን የኢትዮጵያ ቆንስላዎች እንዲዘጉ እስከመወሰን የደረሰ እርምጃ መውሰዷም አይዘነጋም፤ ምንም እንኳን ሁለቲም ቆንስላዎች እስካሁን ስራቸውን ቢቀጥሉም።
ሞቃዲሾ በቅርቡም በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) ይተካል በተባለው አዲስ የሰላም አስከባሪ ሃይል የማትሳተፈው ብቸኛዋ ሀገር ኢትዮጵያ መሆኗን ማስታወቋ የሚታወስ ነው።