ከአንታርክቲካ ድረስ እየመጡ ባለበት ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን መፈለጓ እንደ ስህተት መቆጠር የለበትም- የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር
የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በአንድ ዓመት ውስጥ ለኢትዮጵያ ምን ጥቅም አስገኘ?
ለሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቆም ምክንያት የሆነው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ አንድ ዓመት ሞልቶታል
ከአንታርክቲካ ድረስ እየመጡ ባለበት ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን መፈለጓ እንደ ስህተት መቆጠር የለበትም ሲል የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
ከአንድ ዓመት በፊት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በፌደራል መንግሥት እና ትግራይ ሀይሎች መካከል የተካሄደው የሰላም ስምምነት በዛሬው ዕለት ተፈርሟል።
ይህ ስምምነት ለሁለት ዓመት የተካሄደውን ደም አፋሳሽ እና አውዳሚ ጦርነት ያስቆመ ሲሆን ጦርነቱ ከመቆሙ ውጪ ምን ስኬት ተመዘገበ? በሚል ለውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።
አምባሳደር መለስ በምላሻቸውም " ስምምነቱ በሁለቱ ወገኖች መካከል ጦርነት እንዲቆም ከማድረግ በተጨማቲ ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አቅሟ እንዲመለስ፣ እንደ አየርላንድ እና መሰል ሌሎች ሀገራት ጋር የነበራት የዲፕሎማሲ መሻከር እንዲስተካከል አድርጓል" ብለዋል።
- ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን ለመጠቀም እንደምትደራደር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናገሩ
- ስለባህር በር የሚደረጉ ንግግሮች ግራ አጋቢ እንደሆኑበት የኤርትራ መንግስት ገለጸ
እንዲሁም የስምምነቱ መፈረም እንደ አውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ ካሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገራት እና ተቋማት ጋር መልካም ትብብሮችን መፍጠር አስችሏልም ብለዋል አምባሳደር መለስ።
የስምምነቱ ስኬታማነት በአንድ ዓመት ውስጥ ባሉት ጊዜያት ውስጥ ብቻ የሚወሰን አይደለም የሚሉት አምባሳደር መለስ በቀጣይ ጊዜዎች ቀሪ የስምምነቱ ትግበራዎች እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
ሌላኛው በዛሬው መግለጫ ላይ የተነሳው ጉዳይ የኢትዮጵያ የወደብ ጉዳይ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ጠቅላይ ሚንስትሩ ያነሱት የቀይ ባህር ወደብ ጉዳይ ዙሪያ ያለው አመለካከት ምንድን ነው? በሚል ከጋዜጠኞች ጥያቄ ተነስቷል።
ቃል አቀባዩ በምላሻቸውም "ጠቅላይ ሚንስትሩ የሀገሪቱ የመጀመሪያው ውጪ ጉዳይ ግንኙነት የሚመለከታቸው መሪ ናቸው ነገር ግን በወደብ ጉዳይ ያደረጉት ንግግር በስህተት ተተርጉሟል" ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ በፊትም አማራጭ ወደብ እንዲኖራት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ስትሰራ ነበር የአሁኑ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ንግግርም ለጋራ ጥቅም በትብብር እንስራ ነው ሲሉም ጠቅሰዋል አምባሳደር መለስ።
"ከአንታርክቲካ ድረስ ወደ ቀይ ባህር የመጡ አካላት ባሉበት ሁኔታ ኢትዮጵያ አጠገቧ ያለው ቀይ ባህርን መፈለጓ ስህተት ሊሆን አይችልም" ሲሉም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል ።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሳምንት በተከበረው የሀገር መከላከያ ቀን ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የትኛውንም ሀገር አጥቅታ እንደማታውቅ እና አሁንም ሀይልን የመጠቀም ፍላጎት እንደሌላት መናገራቸው ይታወሳል።