የእስራኤል ታንኮች ከማዕከላዊ ጋዛ ሲያፈገፍጉ፣ 30 ሰዎች ደግሞ በአየር ጥቃት ተገደሉ
የህክምና ባለሙያዎች እንደተናገሩት በጋዛ ከሚገኘው ኑሴራት ካሜፕ ሰሜናዊ ክፍል 19 አስከሬኖችን ተቀብለዋል
በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ በኳታር፣ በግብጽ እና በአሜሪካ ሲደረግ የነበረው ጥረት አሁን ላይ ምንም ፍሬ ሳያፈራ ባለበት ቆሟል
የእስራኤል ታንኮች ከማዕከላዊ ጋዛ ሲያፈገፍጉ፣ 30 ሰዎች ደግሞ በአየር ጥቃት ተገደሉ።
የእስራኤል ታንኮች ይዘውት ከነበረው ማዕከላዊ ጋዛ ካፈገፈጉ በኋላ የእስራኤል ጦር በጋዛ ሰርጥ ሌሊቱን በፈጸመው የአየር ጥቃት አብዛኞቹ የኑሴራት ካምፕ ነዋሪ የሆኑትን ጨምሮ 30 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጤና ባለሙያዎች ተናግረዋል።
የህክምና ባለሙያዎች እንደተናገሩት በጋዛ ከሚገኙት ለረጅም ጊዜ ካገለገሉት ስምንት መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ አንዱ ከሆነው የኑሴራት ካሜፕ ሰሜናዊ ክፍል 19 አስከሬኖችን ተቀብለዋል።
የተወሰኑ ታንኮች ከካምፑ ምዕራባዊ ክፍል የሚንቀሳቀሱ ሲሆን የፍልስጤሙ የሲቪል የአደጋ ጊዜ አገልግሎት በቤታቸው ታፍነው ድረሱልን ለሚሉ ሰዎች መድረስ አለመቻሉን ገልጿል።
ባለሙያዎቹ ሌሎቹ የተገደሉት በጋዛ ሰርጥ ሰሜናዊ እና ደቡባዊ ቦታዎች ነው ብለዋል። የእስራኤል ጦር አዲስ መግለጫ ባይሰጥም፣ በትናንትናው እለት ግን ጦሯ በጋዛ ሰርጥ "የሽብር ኢላማዎችን" መትቷል ብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል ባለስልጣናት በጋዛ እያካሄዱ ባሉት የማጥቃት ዘመቻ ወቅት የያዟቸውን 30 ፍልስጤማውያን ለቀዋል።
የህክምና ባሉሙያዎች እንዳሉት የተለቀቁት ሰዎች ለህክምና ምርመራ በደቡብ ጋዛ ወደሚገኘው ሆስፒታል ደርሰዋል። ከእስር የተለቀቁት ፍልስጤማውያን በእስራኤል እጅ በነበሩበት ወቅት የማሰቃየት ተግባር ይደርስባቸው እንደነበር ተናግረዋል።
በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ በኳታር፣ በግብጽ እና በአሜሪካ ሲደረግ የነበረው ጥረት አሁን ላይ ምንም ፍሬ ሳያፈራ ባለበት ቆሟል።
ከጋዛው ጦርነት በተጓዳኝ ሲደረግ የነበረው የእስራኤል -ሄዝቦላ ጦርነት በአሜሪካ እና ፈረንሳይ አደራዳሪነት በተደረስ የተኩስ አቁም ስምምነት ከረቡዕ ጀምሮ ቆሟል። እስራኤል-ሀማስ ጦርነት እስካሁን 44ሺ በላይ ሰዎች እንዲገደሉና ሁሉም የጋዛ ነዋሪዎች ቢያንስ አንድ ጊዜ ከቤታቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል።
የእስራኤል-ሀማስ ጦርነት የተቀሰቀሰው፣ ሀማስ ጥቅምት 7፣2023 በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመክፈት 1200 ሰዎችን ከገደለ እና ሌሎች 25ዐ ሰዎችን አግቶ ከወሰደ በኋላ ነው።