የጁባላንድ ክልል ከሶማሊያ ፌደራል መንግስት ጋር ያላትን ግንኙነት ማቋረጧን አስታወቀች
የጁባላንድ ክልል ፍድር ቤት በሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ ላይ የእስር ማዘዣ አውጥቷል
የሶማሊያ ፌደራል መንግስት በጁባላንድ ፕሬዝዳንት ማዶቤን በሀገር ክህደት በመክሰስ የእስር ማዘዣ አውጥቶባዋል
ከሶማሊያ የፌዴራሉ መንግስት አባል ግዛቶች አንዷ የሆነችው የጁባላንድ ክልል ከፌደራል መንግስት ጋር ያላትን ግንኙነት ማቋረጧን አስታወቀች።
የጁባላንድ ክልላዊ መንግስት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ትናንት በወጣው መግለጫው፤ በሞቃዲሾ ለሚገኘው የፌዴራል መንግስት የሰጠውን እውቅና ማንሳቱን እና ግንኙነቱን ማቋረጡን በይፋ አስታውቋል።
የጁባላንድ ክልላዊ መንግስት “የሶማሊያ ፌደራል መንግስት ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃመድን ስልጣንን ያለ አግባብ ተጠቅመዋል፣ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በመጣስ የተለያዩ ወንጀሎችን ፈጽመዋል እንዲሁም ከአልሸባብ የሽበር ቡድን ጋር በመበተባበር ሰላምን ለማናጋት እየሰሩ ነው” በሚል ከሷል።
የጁባላንድ ክልላዊ ፍርድ ቤት በትናትናው እለት ምሽት ላይ በሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃመድ ላይ የእስር ማዘዣ አውጥቷል።
በሶማሊያ ፌደራል መንግስት እና በጁባላንድ አስተዳደር መካከል አለመግባባት የተፈጠረው ጁባላንድ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ያደረገችው ምርጫ ተከትሎ ነው።
በክልሉ በተካሄደው ምርጫ ጁባላንድን ከፈረንጆቹ 2013 ጀምሮ የመሩት የፕሬዚዳንት አህመድ መሐመድ ኢስላም (ማዶቤ) ለሶስተኛ ጊዜ መመረጣቸው ተነግሯል።
ይህንን ተከትሎም መቀመጫውን ሞቃዲሾ ያደረገው የሶማሊያ ፌደራል መንግስት፤ በጁባ ላንድ የተካሄደው ምርጫ ያለ ፌደራል መንግስት እውናና ተሳትፎ የተደረገ ነው በሚል ውድቅ አድርጎታል።
ይህንን ተከትሎም በሞቃዲሹ የሚገኝ ፍርድ ቤት በጁባላንድ መሪ ማዶቤን በሃገር ክህደት እና ሕገ መንግስቱን የሚፃረር ተግባር በመፈጸም ክስ በመመስረት የእስር ማዘዣ አውጥቶባቸዋል።
የሶማሊያ የፌዴራል መንግስት ወደ ጁባላንድ ሰራዊቱን መላኩም ነው የተነገረው።
በጁባልንድ ፕሬዚዳንት ማዶቤ የፌደራሉ መንግስት በተረጋጋችው የጁባላንድ ግዛት የፀጥታ ችግር እንዲፈጠር እያደረገ ነው ሲሉ ወንጅለዋል።
የጁባላንድ ወታደሮች ከፍተኛ መስዋእትነት በመክፈል ከዓመታት ግጭት በኋላ ማምጣት የቻሉትን ሰላም በፌደራሉ መንግሥት እየተበጠበጠ እንደሆነም ነው የፕሬዚዳንት ማዶቤ አስተዳደር ያስታወቀው።
ከሶማሊያ የፌዴራሉ አባል ግዛቶች አንዷ የሆነችው ፑንትላንድም ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ከሶማያ ፌዴራል መንገረስት ጋራ ያላትን ግንኙነት ማቋረጧ ይታወሳል።