ተመድ፤ በሊቢያ ታስረው የሚገኙ ሴቶች እና ህፃናት ‘በአስጊ ሁኔታ ላይ’ እንደሚገኙ ገለጸ
የሊቢያ ባለስልጣናት ጅምላ አፈሳው “የተደራጁ ወንጀለኞች እና የህገ-ወጥ እጽ አዘዋዋሪዎችን” ዒላማ ያደረገ ነው ብለዋል
የሊቢያ ባለሥልጣናት ትሪፖሊ ውስጥ ባካሄዱት አፈሳ ከ5 ሺህ የሚበልጡ ስደተኞች እንደታሰሩ የድርጅቱ መረጃ ያመለክታል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት ፈንድ (ዩኒሴፍ) በሊቢያ የስደተኞች ማቆያ እስር ቤቶች የሚገኙ ከ 1 ሺህ በላይ ሴቶችና ህጻናት “በአስጊ ሁኔታ ላይ” እንደሚገኙ ገለጸ ፡፡
ዩኒሴፍ ባወጣው መግለጫ በዚህ ወር ብቻ በሊቢያ 255 ህጻናትን ጨምሮ 751 ሴቶች ስደተኞችና እና ጥገኝነት ፈላጊዎች በእስር ቤቶች ታጉረው ይገኛሉ ብሏል፡፡
አይ ኦ ኤም፤ የኢትዮጵያ ዳይሬክተሩን ‘ያልተፈቀደ’ ቃለ መጠይቅ ማድረጋቸውን ተከትሎ ወደ ዋና መስሪያ ቤቱ ጠራ
በስደተኞች ማቆያ እስር ቤቶቹ “አምስት ከቤተሰቦቻቸው የተነጠሉ ልጆች እና ቢያንስ 30 ሕፃናት ይገኙበታል”ም ነው ዩኒሴፍ ያለው፡፡
ዩኒሴፍ በመግለጫው “የሴቶቹና ህጻናት ደህንነት አደጋ ላይ ነው” ሲልም አስጠንቅቋል፡፡
በሊቢያ የዩኒሴፍ ተወካይ ክሪስቲና ብሩግዮሎ“ በሊቢያ የሚገኙ ስደተኞች እና ስደተኛ ልጆች የዘፈቀደ እስርን ጨምሮ ከባድ የሕፃናት መብት ጥሰቶች ይደርሱባቸዋል” ሲል ተናግሯል፡፡
ተወካዩ በእነዚህ እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ልጆች በ“አሰቃቂ እና ኢ-ሰብአዊ” በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙም አክሏል፡፡
አል-ማባኒ እስር ቤት በሊቢያ ካሉ የአስር ማቆያ ማእከላት ትልቁ ሲሆን በውስጡ መያዝ ከሚችለው አራት እጥፍ በላይ የሚሆኑ 5 ሺህ ስደተኞች ታጉረው የሚገኙበት ስፍራ ነው እንደ ዩኒሴፍ ገለጻ፡፡
ዩኒሴፍ የሊቢያ ባለስልጣናትን “የልጆችን ደህንነት የመጠበቅና እና ከወላጆቻቸው ፣ ከአሳዳጊዎቻቸው እንዲሁም ከቤተሰቦቻቸው እንዳይለዩ የማድረግ ሃላፊነት አለባቸው” ሲል አሳስባል።
የሊቢያ ባለሥልጣናት በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ትሪፖሊ ውስጥ መደበኛ ያልሆኑ ስደተኞች ላይ ያነጣጠረ አፈሳ ማካሄዳቸውን ተከትሎ በርካቶች በእስር ቤቱ ታጉረው ይገኛሉ፡፡
የድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ በጅምላ አፈሳው እስካሁን ከ5 ሺህ የሚበልጡ ስደተኞች ሳይታሰሩና ለአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሳይጋለጡ አልቀረም፡፡
ዩኒሴፍ እና ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድኑ አፈሳው አደገኛና በርካቶችን ለእስር የዳረገ ነው ቢሉም፤ የሃገሪቱ ባለስልጣናት ግን አስተባብለውታል፡፡
እርምጃው “የተደራጁ ወንጀለኞችን እና ህገ-ወጥ እጽ አዘዋዋሪዎችን” ዒላማ ያደረገ ነው በሚል በመከራከርም ላይ ናቸው፡፡
እንዲያውም ባለስልጣናቱ በተፈጠረው ትርምስ መሃል 2 ሺህ የሚጠጉ ስደተኞች አምልጠውናል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
በሊቢያ የተመድ ሚሽን እንዳስታወቀው ከሆነ በተወሰደው እርምጃ የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ 15 ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡
ኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተዋል ያለቻቸውን 7 የተመድ ሰራተኞች በ72 ሰዓታት ሃገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አሳሰበች
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ተቋም (አይ ኦ ኤም) በበኩሉ ጅምላ አፈሳውን ተከትሎ ባለፈው ሳምንት ትሪፖሊ የሚገኘው የአል-ማባኒ እስር ቤት ጠባቂዎች በወሰዱት እርምጃ ስድስት ስደተኞችን ተኩሰው ሲገድሉ 24 ሰዎች አቁስለዋል ሲል አስታውቋል።
አፈሳውን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በአይ ኦ ኤም የሊቢያ ቢሮ ደጃፍ ሰልፍ አድርገዋል፡፡
አይ ኦ ኤም ትናንት ባወጣው መግለጫ የስደተኞቹ ስቃይ ያሳስበኛል ማለቱ ይታወሳል፡፡