ሞስኮ እና ኪቭ የኒውክለር ጣቢያውን በሚመለከት ውዝግብ ውስጥ ናቸው
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) የኒውክለር ተቆጣጣሪ ቡድን ዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ጣቢያ መድረሳቸው ተገለጸ፡፡
የኒውክለር ጣቢው በዩክሬን የሚገኝ ሲሆን አሁን ላይ በሩሲያ ኃይሎች መያዙ እያነጋገረ ነው፡፡ ወደ ስፍራው ያቀናው ቡድን በዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ማሪያኖ ግሮሲ የተመራ ነው፡፡
ይህ የኒውክለር ጣቢያ በአውሮፓ ትልቁ ሲሆን ይህንን የመጠበቅ ኃላፊነት የዓለም ሕዝብ ሊሆን ይገባል እየተባለ ነው፡፡ የኒውክለር ጣቢያውን ደህንነት ለመጠበቅ ወደ ስፍራው ያቀናው ቡድን ዩክሬን ደርሷል ተብሏል፡፡ በኤጄንሲው ዋና ዳይሬክተር የሚመራውና ወደ የኒውክለር ጣቢያው ያቀናው ቡድኑ ዛሬ ወደ ኪቭ መድረሱም ነው የተገለጸው፡፡
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሌባ፤ የተመድ የኒውክለር ተቆጣጣሪ ቡድን በዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ጣቢያ የሚያደርገው ቁጥጥር በታሪክ ከባዱ ኃላፊነት እንደሆነ ገልጸዋል ተብሏል፡፡ ሚኒስትሩ፤ የግሮሲ ቡድን የተሰጠው ተልዕኮ በኒውክለር ተቆጣጣሪ ቡድኑ ታሪክ ትልቁና ከባዱ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
ሩሲያ፤ ዩክሬንን ብቻ ሳይሆን ዓለምን በሙሉ ችግር ውስጥ እየከተተች እንደሆነ ያስታወቁት የዩክሬኑ ባለስልጣን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይህንን የሞስኮን ድርጊት በጋራ መመከት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ ዓለም በጋር ትብብሩ የሩሲያን ጦር ከኒውክለር ጣቢያው ማስወጣት እንዳለበትም ነው የተገለጸው፡፡
ዩክሬን አሁን ላይ ቡድኑን እየመሩ ኪቭ ከደረሱት የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ማሪያኖ ግሮሲ እና ከቡድናቸው አስተያየቶችን እየጠበቀች መሆኑንም የውጭ ጉዳይ ሚኒትሯ ተናግረዋል፡፡
የኒውክለር ጣቢያው በሩሲያ ጦር ቁጥጥር ስር ሲሆን ምዕራባውያን ለዩክሬን እንዲሰጥ እየወተወቱ ቢሆንም ሞስኮ ግን ፈቃደኛ ሳትሆን ቀርታለች፡፡ አሁን ላይ በኒውክለር ጣያቢው አካባቢ የተኩስ ልውጥ እየተካሄደ ሲሆን ጣቢያው ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ዓለም አቀፍ ጥሪዎች እየተሰሙ ነው፡፡ ወደ ስፍራው ያቀናው ቡድን በአካባቢው ያለውን ጉዳት እንዲሁም የደህንነትና የጸጥታ ሁኔታን እንደሚመለከት ይጠበቃል፡፡
ሞስኮ እና ኪቭ የኒውክለር ጣቢያውን በሚመለከት ውዝግብ ውስጥ ከገቡ ቀናት የተቆጠሩ ሲሆን የቡድን ሰባት አባል ሀገራትም ከዩክሬን ጎን ሆነው እየተከራከሩ ነው፡፡