አሜሪካ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደርን ከሀገሯ አባረረች
በዋሸንግተን የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ተሳድበዋል በሚል ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ታዘዋል ተብሏል

አሜሪካ የሀገር ዲፕሎማትን ስታባርር ከረጅም ጊዜ በኋላ ነው
አሜሪካ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደርን ከሀገሯ አባረረች፡፡
የዓለማችን ቁጥር አንድ ልዕለ ሀያል ሀገር የሆነችው አሜሪካ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደርን ዋሸንግተንን ለቀው እንዲወጡ አዛለች፡፡
የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በኤክስ አካውንታቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ እንዳሉት “በዋሸንግተን የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር እዚህ አይፈለጉም” ብለዋል፡፡
በአሜሪካ የዋሸንግተን አምባሳደር ኢብራሂም ራሱል ደቡብ አፍሪካ ካሏት አንጋፋ ዲፕሎማቶች መካከል አንዱ ሲሆን ከ2010 እስከ 2015 ድረስ በዋሸንግተን የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ሆነው አገልግለው ነበር፡፡
በድጋሚ ከ2025 ጀምሮ ሀገራቸውን በአምባሳደርነት እንዲያገለግሉ ተሹመው የነበሩት አምባሳደር ራሱል ከፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳድር ጋር ግጭት ውስጥ ገብተዋል፡፡
አምባሳደሩ ከሰሞኑ በበይነ መረብ በተካሄደ አንድ ሴሚናር ላይ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የነጭ የበላይነትን ለማንበር የሚሰራ እና መድሎዎች እንዲኖሩ የሚሰራ ፖለቲከኛ ነው የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ይህን ተከትሎም አምባሳደር ራሱል በአሜሪካ መቆየት የሚያስችላቸውን የዲፕሎማሲ ፈቃድ የተሰረዘ ሲሆን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ተነግሯቸዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ በውሳኔው ማዘኑን ገልጾ ከአሜሪካ ጋር ጥብቅ እና የጋራ ተጠቃሚነት ያለው ወዳጅነት ለመመስረት እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡
አሜሪካ የሀገራትን አምባሳደር የማባረር ልምድ የሌላት ሲሆን በተለይም ከቀዝቃዛው ጦርነት ጊዜ ጀምሮ ሽኩቻ ውስጥ ከነበረችባቸው ሩሲያ እና ሌሎች ሀገራትን አምባሳደሮች አላባረረችም ነበር፡፡
የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳድር በደቡብ አፍሪካ ላይ ጫና ያሳደረው የነጮችን መሬት እየቀማች ነው በሚል ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ ግን ይህን ክስ በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጋለች፡፡