በደቡብ አፍሪካ ምርጫ የፕሬዝዳንት ራማፎሳ ኤኤንሲ ፓርቲ መንግስት መመስረት የሚያስችለውን ድምጽ ሳያገኝ ቀረ
97 በመቶ የድምጽ ቆጠራው የተጠናቀቀ ሲሆን እስካሁን ባለው ውጤት ኤኤንሲ ፓርቲ 40 በመቶ ድምጽ አግኝቷል
ፓርቲው 50 በመቶ እና ከዛ በላይ ድምጽ ካላገኝ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ጥምር መንግስት ለመመስረት ይገደዳል
በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው ፓርላመንታዊ ምርጫ ለ30 አመታት በስልጣን ላይ የቆየው የኔልሰን ማንዴላ አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ (ኤኤንሲ) በታሪኩ ለመጀመርያ ግዜ ዝቅተኛውን ድምጽ አግኝቷል።
ዛሬ የወጡ መረጃዎች በ23ሺ የምርጫ ጣብያዎች በተደረገው ምርጫ የድምጽ ቆጠራው 97 በመቶ መጠናቀቁን የገለጹ ሲሆን በዚህ ውስጥ ኤኤንሲ ፓርቲ ማግኝት የቻለው ድምጽ 40.14 በመቶ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሮይተርስ አንደዘገበው ዴሞክራቲክ አሊያንስ 21.7፣ በቀድሞው ፕሬዝዳነት ጃኮብ ዙማ የሚመራው ኤምኬ ፓርቲ 14.8 ሲያገኝ፣ የማርክሲስት ርዕዮት የሚያቀነቅነው ኢኤፍ ኤፍ ፓርቲ 8 በመቶ ድምጽ ማገኝት ችሏል።
በ6 የምርጫ ዘመኑ እጅግ ዝቅተኛ የተባለውን ድምጽ ያገኝው የሲሪል ራማፎሳ ፓርቲ በባለፈው ምርጫ 57 .5 በመቶ ድጋፍ በማግኝት በስልጣን ላይ ዘልቋል።
ከላተቆጠረው 3 በመቶ ድምጽ ብቻውን መንግስት ለመመስረት የሚያስችለውን ድምጽ ካላገኝ ደግሞ ከሌሎች በርዕዮት ከማይመሳሰሉት ፓርቲዎች ጋር ጥምር መንግስት ለመመስረት ይገደዳል።
የመጨረሻ የምርጫው ውጤት በነገው እለት የሚታወቅ ቢሆንም ተንታኞች ኤኤንሲ ፓርቲ ከየትኛው ፓርቲ ጋር ጥምር መንግስት ሊመሰርት እንደሚችል ሀሳባቸውን እየሰጡ ነው፡፡
ፓርላመንታዊ ስርአትን በምትከተለው ደቡብ አፍሪካ ዜጎች ፓርቲዎችን ከመረጡ በኋላ ምክር ቤት የሚገቡ ፓርቲዎች ፕሬዝዳንቱን ይሰይማሉ።
በዚህኛው ምርጫ አብዘሀኛውን የፓርላማ መቀመጫ መያዝ ያልቻለው ኤኤንሲ ራማፎሳን ድጋሚ ፕሬዝዳንት አድርጎ ለማስመረጥ የሌሎች ፓርቲዎችን ይሁንታ ማግኝት ይጠበቅበታል።
ከየትኛው ፓርቲ ጋር ጥምር መንግስት እንደሚመሰርት ያልወሰነው ኤኤንሲ የመጨረሻ ውጤቱ በተገለጸ በ14 ቀናት ውስጥ በፓርላማው ቀርቦ የመንግስት ምስረታውን ማከናወን ይኖርበታል።
ከ30 አመታት በኋላ በሀገሪቱ ትልቅ የፖለቲካ አሰላለፍ ለውጥ አምጥቷል በተባለው ምርጫ ሁለተኛውን ከፍተኛ ድጋፍ ያገኝው ዴሞክራቲክ አሊያንስ ፓርቲ መሪው ጆን ስቴንሆዜን ፤ከራማፎሳ ፓርቲ ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው ነገር ግን ከሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በጉዳዩ ላይ እንደሚመክሩበት ተናግረዋል።
በእርግጥ ኤኤንሲ የተሻሉ የሚላቸውን አጣምሪዎች ለመምረጥ የመጨረሻ ውጤቱን መጠበቅ ይኖርበታል እስከ ሀምሳ በመቶ ድምጽ ማግኝት የሚችል ከሆነ እነስተኛ ድምጽ ያላቸውን ፓርቲዎች ጋር መንግስት በመመስረት ተጽእኖውን አስጠብቆ መጓዝ ይችላል።