ቀጣዩ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ለመሆን እየተፎካከሩ የሚገኙት እጩዎች እነማን ናቸው?
ከሳምንት በኋላ የሚደረገው ምርጫ ከአፓርታይድ ማብቃት በኋላ ከፍተኛ ፉክክር የሚደረግበት ምርጫ ስለመሆኑ እየተነገረለት ነው
ኤኤንሲ ፓርቲ ከረጅም ግዜ በኋላ በዚህኛው ምርጫ ሊሸነፍ የሚችልበት እድል እንዳለ ከህዝብ የተሰበሰቡ አስተያየቶች አመላክተዋል
በመጭው ሳምንት እሮብ የሚደረገው የደቡብ አፍሪካ ምርጫ የሀገሪቷን የፖለቲካ ቅርጽ ሊቀይር የሚችል ውጤት ሊመዘግብት እንደሚችል በርካቶች እየተናገሩ ነው፡፡
ያለፉትን 30 አመታት በስልጣን ላይ የቆየው የሲሪል ራማፎሳ ኤኤንሲ (አፍሪካ ናሽናል ኮንግረንስ) ፓርቲ ምርጫውን እንደሚያሸንፍ ከፍተኛ ግምት ቢያገኝም በዘንድሮው ምርጫ ቀላል የማይባል ድምጽ ሊያጣ እንደሚችልም ተነግሯል፡፡
ፓርቲው በስልጣን ለመቆየት የሚያስችለውን ድምጽ ካለገኝ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በመቀናጀት ጥምር መንግስት የሚመሰርት ይሆናል፡፡
የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ለምርጫ እንዳይወዳደሩ በፍርድ ቤት ታገዱ
በዘንድሮው ምርጫ ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸው እጩዎች እና ፓርቲዎች እነማን ናቸው?
1. ሲሪል ራማፎሳ (ኤኤንሲ)
የ71 አመቱ ራማፎሳ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ1980ዎቹ ጀምሮ ነው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመሩት።በ1991 ደግሞ የኤኤንሲ ፓርቲ ዋና ጸሀፊ ሆነው ሰርተዋል፡፡
በዚህ ወቅት በአብዛሀኛው በአናሳ ነጮች ይመራ ከነበረው አስተዳደር ጋር በስልጣን ክፍፍል እና በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ዙርያ የተደረገውን ድርድር መርተዋል፡፡
1996 በኔልሰን ማንዴላ የፕሬዝደንትነት ዘመን ከፖለቲካው አለም ራሳቸውን ያገለሉት ራማፎሳ በቢዝነሱ አለም ውስጥ በመግባት በሀገሪቷ ስመጥር ባለጸጋ መሆን ችለዋል፡፡
በ2017 የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ተክተው ወደ ስልጣን እና ፖለቲካ የተመለሱት አሁናዊው ፕሬዝዳነት ወጥ የሆነ የአመራረር አቋም የላቸውም በሚል በፓርቲያቸው እና በአንዳንድ ፓርቲው ደጋፊዎች ዘንድ ይታማሉ፡፡ ይህም ሆኖ በዚህኛው ምርጫ የማሸነፍ ቅደመ ግምት ከተሰጣቸው እጩዎች መካከከል ቀዳሚው ናቸው
2. ጆን ሴትንሆዜን (ዴሞክራቲክ አሊያንስ)
ፖለቲካን በወጣትነት እድሜያቸው የጀመሩት የ48 አመቱ ጎልማሳ ከተፎካካሪዎች መካከል በቆዳ ቀለማቸው ነጭ የሆኑ ብቸኛው እጩ ናቸው፡፡ የ ‘’ዲኤ’’ ፓርቲ የደርባን ከተማ ተወካይ ሆነው ምክር ቤት የገቡት በ22 አመታቸው ነበር፡፡
በሂደት በፓርቲው ሀላፉነት እያደጉ የመጡት ሴትንሆዜን በ2019 የፓርቲያቸው ሊቀመንበር መሆን ችለዋል፡፡ ፓርቲያቸው ለነጮች ያደላል በሚል በተደጋጋሚ ወቀሳ የሚነሳበት ሲሆን እሳቸው ግን ለዴሞክራሲ እና እኩልነት የቆምን ነን ሲሉ ይከራከራሉ፡፡
3. ጁሊየስ ማሌማ (ኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ)
ራሱን ፓንአፍሪካኒስት ብሎ የሚጠራው ማሌማ በእድሜ ከሁሉም እጩዎች ትንሹ ነው፡፡ የቀድሞው የኤኤንሲ ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ መሪው ማሌማ በማህበረሰቡ ውስጥ ክፍፍል በመፍጠር በሚል በ2011 ከፓርቲው ታግዷል፡፡ ከዚያ ቀጥሎ “ኢኤፍኤፍ” ፓርቲን መስርቶ የተለያዩ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ የማርክሲስት ርዕዮትን የሚከተለው ባሌማ በነጮች የተያዙ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ነጥቆ ለጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያን አርሶአደሮች መከፋፈል አለበት ሲል በተደጋጋሚ ይደመጣል፡፡
በሀገሪቱ አሳሳቢ ከሚባሉ ጉዳዮች መካከከል አንዱ በሆነው የስደተኞች ጉዳይ ላይም ለየት ያለ አቋም አለው። ሌሎች ፓርቲዎች የስደተኛ ፖሊሲው ጠበቅ ማለት አለበት ሲሉ ማሌማ በተቃራኒው አፍሪካዊያን በአፍሪካ ውስጥ በነጻነት መንቀሳቀስ አለባቸው ባይ ነው፡፡
4. ጃኮብ ዙማ (ኡሙኩንቶ ዊሲዝዋ)
በዚህኛው ምርጫ “ኤምኬ” ፓርቲን ወክለው ሊወዳደደሩ የነበሩት ዙማ የሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በጣለባቸው እገዳ ከእጩ ዝርዝር ውስጥ ወጥተዋል፡፡ ሆኖም ከተመሰረተ አመት ያልተሸገረው ፓርቲያቸው ከፍተኛ ግምት ካገኙት ውስጥ ተካቷል:: በዙማ የትውልድ መንደር እና በሌሎች ውጤት ወሳኝ ናቸው በተባሉ አካባቢዎች ጥቂት የማይባሉ ደጋፊዎችን ማግኝት ችሏል፡፡
በዚህ ምርጫ ቅድመ ግምት የተሰጣቸው እጩ ፓርቲዎች ባያሸንፉ እንኳን የራማፎሳው ኢኤንሲ ፓርቲ ጥምር መንግስት ለመመስረት እንዲገደድ የሚያደርገውን ድምጽ እንደሚሻሙት እየተነገረ ነው።