የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ለምርጫ እንዳይወዳደሩ በፍርድ ቤት ታገዱ
የደቡብ አፍሪካ ህግ በወንጀል የተከሰሰ ሰው ለፓርላማ መቀመጫ እንዳይወዳደር ይደነግጋል፡
አወዛጋቢው የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት በቀጣይ ሳምንት በሚደረገው አጠቃላይ ምርጫ እንዳይሳተፉ በከፍተኛው ፍርድ ቤት እግድ ተጥሎባቸዋል
በቀድሞው የዙማ አስተዳደደር ላይ የቀረበውን የሙስና ክስ ሲመረምር ለነበረው ፍርድ ቤት በአካል ቀርበው ቃላቸውን ለመስጠት ፍቃደኛ ያልሆኑት ፕሬዝዳንቱ ችሎት በመድፈር በ2021 የ15 ወራት እስር ተፈርዶባቸው ነበር።
ሁለት ወራትን በእስር ቤት ያሳለፉት ዙማ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በደቡብ አፍሪካ እያጋጠመ ያለውን የእስር ቤቶች መጨናነቅ ለመቀነስ ከፍተኛ ወንጅል ላለሰሩ ታሳሪዎች ባደረጉት ይቅርታ ከእስር መፈታታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኡሞኮንቶ ዊሲዙዋ (ኤም ኬ) የተሰኝ ፓርቲ መስረተው ለፓርላማ መቀመጫ የምረጡኝ ቅስቀሳ ሲያድርጉ፣ ብዙዎች ከ2009-2018 በስልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ፈጽመውታል የተባለውን የሙስና ክስ በማንሳት ያለፈው ሊደገም ነው ሲሉ ተሳልቀዋል፡፡
ይህ ቢሆንም ዙማ ጥቂት የማይባል ደጋፊ ያላቸው አንጋፋ ፖለቲከኛ ናቸው፡፡
ሁለት የምርጫ ዘመናቸውን ካሸነፉበት ኤ ኤን ሲ ፓርቲ ከተለያዩ በኋላ አዲስ በተቀላቀሉት ኤም ኬ ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበሩት የ82 አመቱ አዛውንት በከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ የማይሉት የመጨረሻ ውሳኔ እንደተላለፈባቸው ነው የተሰማው፡፡
የሀገሪቱ ህገ መንግሰት በወንጀል የተከሰሰ እና ከአንድ አመት በላይ የእስር ውሳኔ የተላለፈበት ማንኛውም ግለሰብ በፓርላማም ሆነ በምርጫ እንዳይሳተፍ ይደነግጋል፡፡
ባሳለፍነው መሰክረም የፓርቲ እውቅና ያገኘው ኤም ኬ ፓርቲ የዋና ዕጩውን ከምርጫ መሰረዝ ተከትሎ ባወጣው መግለጫ የፓርቲውን አሸናፊነት አይቀይረውም ሌሎች ብዙ መሪዎች አሉን ብሏል።
ፓርቲው በዙማ የትውልድ መንደር ኩዋ ዙሉ ናታል ከፍተኛ ድጋፍ ያለው ሲሆን የኢኮኖሚ ማዕከል ነጭ በምትባለው ጋውታንግም በርካታ ደጋፊዎች አሉት፡፡
እነዚህ አካባቢዎች ደግሞ ባለፉት አመታት የደቡብ አፍሪካን ምርጫ ውጤት በመወሰን ከፍተኛ አቅም ያላቸው እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡
ከ8 ቀናት በኋላ እንደሚካሄድ በሚጠበቀው ምርጫ የደቡብ አፍሪካ ዙማ የተቀላቀሉት አዲሱ ኤ ም ኬ ፓርቲ የራማፎሳን ኤ ኤን ሲ ፓርቲን የመገዳደደር አቅም እንዳለው ከፍተኛ ግምት አግኝቷል፡፡
በምርጫው የፓርላማ አባላት እና የክልል ተወካዮች የሚመረጡ ሲሆን የፓርላማ አባላቱ ፕሬዝዳንቱን ይሰይማሉ።
ከህዝብ የተሰበሰቡ የቅድመ ምርጫ ውጤቶች ከ30 አመታት በኋላ እድሜ ጠገቡን ኤ ኤን ሲ ፓርቲን በብርቱ የሚፎካከር ፓርቲ መመስረቱን የሚያሳዩ ናቸው ተብሏል።