28 ሚሊዮን መራጮች ድምጽ ለመስጠት ተመዝግበዋል
ደቡብ አፍሪካዊያን ከማለዳው አንድ ሰአት ጀምሮ በምርጫ ጣብያዎች ይገኛሉ፡፡
በርካታ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ጎልተው በሚደመጡባት ደቡብ አፍሪካ በመከናወን ላይ የሚገኝው ምርጫ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ መልክ ውስጥ አዲስ ነገር የሚታይበት ሊሆን እንደሚችል ከፍተኛ ግምት አግኝቷል፡፡
በ1994 ከአፓርታይድ ሰርአት ማብቃት በኋላ ሀገሪቷን ለሶስት አስርተ አመታት ያስተዳደደረው የኔልሰን ማንዴላ አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ ኤኤንሲ ፓርቲ በዚህኛው ምርጫ የአሸናፊነቱ ነገር ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡
62 ሚልየን ህዝብ በሚገኝባት ሀገር ግማሹ በድህነት ውስጥ የሚኖር ነው፣ በአፍሪካ የተሻሉ ከሚባሉት መካከል አንዱ የሆነው ኢኮኖሚ 32 በመቶ የስራ አጥነት ምጣኔን ይዟል፡፡
ከፍተኛ የኑሮ ልዩነት፣ድህነትእና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ተመርኩዘው የሚነሱ ጥያቄዎች የ30 አመቱ ፓርቲ የስልጣን ቀጣይነት አደጋ ውስጥ እንዲገባ አድርገውታል፡፡
ያለፉትን 6 ምርጫዎችን አሸንፎ በመንበሩ ላይ የዘለቀው ኤኤንሲ በዚህኛው ምርጫ እንደቀደመው ብቻውን የሚያሸንፍበት እድል ጠባብ ስለመሆኑ ከህዝብ የተሰበሰቡ የቅድመ ምርጫ አስተያየቶች ጠቁመዋል፡፡
ፓርቲው በዚህኛው ምርጫ መንግስት ለመመሰረት ከሚያስፈለገው 50 በመቶ ድምጽ በታች ሊያገኝ እንደሚችል አብዘሀኛውን የፓርላማ መቀመጫንም እንደሚያጣ ነው የተነገረው፡፡
በ2019ኙ ምርጫ በ57.5 በመቶ ድምጽ ያሸነፈው ኤኤንሲ አመቱ በታሪኩ ዝቅተኛውን ድጋፍ ያገኝበት ነበር፡፡
ፓርቲው መንግስት ለመመስረት አስፈላጊውን ድምጽ ካላገኝ ጥምር መንግስት ለመመስረት የሚገደድ ይሆናል፡፡
ብርቱ ፉክክር ይደረገብታል በተባለው በዛሬው ምርጫ ለመሳተፍ 28 ሚልየን ዜጎች የምርጫ ካርድ የወሰዱ ሲሆን በ9 ግዛቶች በሚከናወነው ምርጫ 22ሺህ የምርጫ ጣብያዎች ተዘጋጅተዋል፡፡
3ሺህ ወታደሮች የምርጫውን ሰላማዊነት ለማስጠበቅ በመላ ሀገሪቱ የተሰማሩ ሲሆን ፤የሀገሪቱ አሁናዊ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በትውልድ ከተማቸው ጆሀንስበርግ ተገኝተው ድምጽ መስጠታቸው ነው የተዘገባው።
በዚህ ምርጫ ከፍተኛ ግምት ያገኙት ኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተር እና ዴሚክራቲክ አልያንስ ፓርቲዎች ለብቻቸው ስልጣን ለመያዝ የሚያስችል ድምጽ እንደማያገኙ ቢገመትም የራማፎሳን ፓርቲ ጥምር መንግሰት እንዲመሰርት የሚስችል ድጋፍ እንደሚኖራቸው ግን ይገመታል፡፡
ምርጫው ዛሬ ሙሉቀን የሚካሄድ ሲሆን ውጤቱ ደግሞ በመጭው እሁድ ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃ።