የደቡብ አፍሪካ የአለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት መውጣት ውዝግብ
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ትናንት በሰጡት መግለጫ ፓርቲያቸው ከአይሲሲ ለመውጣት መወሰኑን ገልጸው ነበር
የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት በበኩሉ ራማፎሳ “ስህተት ፈጽመዋል” የሚል መግለጫ አውጥቷል
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ሀገራቸው ከአለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት ልትወጣ እንደምትችል በትናንትናው እለት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ፕሬዝዳንቱ በደቡብ አፍሪካ ጉብኝት እያደረጉ ከሚገኙት የፊንላንድ ፕሬዝዳንት ሳውሊ ኒኒስቶ ጋር በሰጡት መግለጫ፥ ደቡብ አፍሪካ ከአይሲሲ መውጣት አለባት ሲሉ ተደምጠዋል።
አይሲሲ ለተወሰኑ ሀገራት ኢፍትሃዊነቱን ማሳየቱን ተከትሎ ገዥው ፓርቲ አፍሪካ ናሽናል ኮንግረንስ (ኤኤንሲ) ከአለማቀፉ ፍርድ ቤት ለመውጣት መወሰኑንም ነበር ፕሬዝዳንቱ በመግለጫቸው ያነሱት።
የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ግን ራማፎሳ በመግለጫቸው የተሳሳተ ነጥብ ማንሳታቸውን በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ መግለጹን ሬውተርስ ዘግቧል።
“ደቡብ አፍሪካ የአይሲሲ ፈራሚ ሀገር ሆና ትቀጥላለች፤ በታህሳስ ወር 2020 በተካሄደው የኤኤንሲ ጉባኤ ከፍርድ ቤቱ ለመውጣት የተያዘው እቅድ ውድቅ መደረጉ ይታወሳል፤ ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ጉባኤም የባለፈው አመት ውሳኔ እንዲጸና ነው የተወሰነው” ብሏል የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት።
ደቡብ አፍሪካ ከአለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለመውጣት ስትዝት ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም።
በፍርድ ቤቱ የእስር ማዘዣ ወጥቶባቸው የነበሩት የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር በ2016 ሀገሪቱን ሲጎበኙ አሳልፋ እንድትሰጥ ተጠይቃ በቁጥጥር ስር ሳታውላቸው መቅረቷ የሚታወስ ነው።
የአለም አቀፉ ፍርድ ቤት ባለፈው መጋቢት ወር በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ የእስር ማዘዣ ማውጣቱን ተከትሎም ይሄው ጉዳይ ዳግም ማነጋገሩን ቀጥሏል።
ፑቲን በነሃሴ ወር በፕሪቶሪያ በሚካሄደው የብሪክስ (ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ) ጉባኤ ይሳተፋሉ መባሉ ደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንቱን አሳልፋ ትሰጣለች ወይ የሚለውን ጥያቄ እያስነሳ ነው።
ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በትናንቱ መግለጫቸው ፑቲንን አሳልፋችሁ ትሰጣላችሁ ወይ ተብለው ተጠይቀው “ጉዳዩን እያጤነው ነው” የሚል አጭር መልስ ሰጥተዋል።
የሞስኮ ጋር ጥብቅ ወዳጅነት ያላት ደቡብ አፍሪካ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ጦርነቱን አላወገዘችም የሚል ቅሬታ በምዕራባውያን ይቀርብባታል።
ከሩሲያ እና ቻይና ጋር ወታደራዊ ልምምድ በማድረግም አሰላለፏን በግልጽ አሳይታለች ይሏታል።
አፍሪካዊቷ ሀገር ግን በጦርነቱ ገለልተኛ አቋም እንዳላት በመግለጽ ወቀሳውን ታስተባብላለች።