ሩሲያ የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ ላይ የእስር ማዘዣ አወጣች
ሩሲያ በፑቲን ላይ እስር ማዘዣ እንዲወጣ ያደረጉት አቃቤ ህግ ካሪም ከሃን በጥብቅ እፈልጋለሁ ብላለች
የወንጀል ፍርድ ቤት ባሳለፍነው መጋቢት ወር በፕሬዝዳንት ፑቲን ላይ የእስር ማዘዣ አውጥቷል
ሩሲያ የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ ላይ የእስር ማዘዣ ማውጠቷ ተገለጸ።
የአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዳኞች ባሳለፍነው መጋቢት ወር በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ የእስር ማዘዣ ማውጣታቸው ይታወሳል።
ፍርድ ቤቱ የእስር ማዘዣ ያወጣው በዩክሬን ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሩሲያ ፕሬዝዳንት ዋነኛው ተጠያቂ ናቸው በሚል ነው።
ይህንን ተከትሎም ሩሲያ በፑቲን ላይ እስር ማዘዣ እንዲወጣ ያደረጉት አቃቤ ህግ ካሪም ከሃን ላይ የእስር ማዠዣ ማውጣቷ ነው የተገለጸው።
መቀመጫውን ዘ ሄግ ያደረገው የአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ ካሪም ከሃን በሩሲያ የሀገር ውስጥ ሚኒስትር የተፈላጊ ዝርዝር ውስጥ መካተታቸው ተነግሯል።
የብሪታኒያ ዜግነት ያላቸው የአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ ካሪም ከሃን ፎቶግራፍም በሩሲያ የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ዳታ ቤዝ ይለቀቃል ነው የተባለው።
ትላቅ ወንጀሎችን የሚከታተለው የሩሲያ የመርማሪዎች ኮሚቴ ባሳለፍነው መጋቢት ወር ላይ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ክስ ጋር በተያያዘ አቃቤ ህግ ከሃን ንጹህ የሆነ ግለሰብን በወንጀል ፈርጀዋል በሚል ጉዳያቸው በህግ እንደሚታይ ማሳወቁ ይታወሳል።
የአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዋነኛው ተጠያቂ ናቸው በሚል ነበር የእስር ማዘዣ ያወጣባቸው።
የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በወቅቱ በሰጠው መግለጫ የዓለም አቀፍ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ትዕዛዝን ውድቅ አድርጓል።
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛራኮቫ እንዳሉት "የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ረብ የለሽ እና የማይተገበር ነው፣ ሩሲያ ባልፈረመችው ህግ ማንም ሊጠይቃት አይችልም" ሲሉ ለራሺያ ቱዴይ ተናግረዋል።