የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ ለፑቲን ደብዳቤ ጻፉ
አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የዩክሬን የጥቁር ባህር እህል ስምምነት የወደፊት መንገድን በሚመለከት ምክረ-ሀሳብ አቀረቡ
ሩሲያ ባለፈው ዓመት የተደረሰው የእህል ስምምነት እንዲቀጥል እንደማትፈልግ ፍንጭ ሰጥታለች
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ለሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬንን እህል ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ወደ ውጭ መላክ የሚያስችለውን ስምምነት ለማሻሻል ደብዳቤ ጽፈዋል።
የተመድ ቃል አቀባይ ጉቴሬዝ ምክረ-ሀሳቡን ለፑቲን እንዲያደርሱ ለሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌ ላቭሮቭ መላካቸውን ተናግረዋል።
ላቭሮቭና ጉተሬዝ በኒዮርክ ተገናኝተው ለ90 ደቂቃ መነጋገራቸውን የተመድ ምክትል ቃል አቀባይ ፈርሀን ሀቅ ተናግረዋል።
ጉቴሬዝ ሩሲያ የራሷን እህል እና ማዳበሪያ ለውጭ ገበያ መላኳን በተመለከተ ያላትን ስጋት መመልከታችንም ተናግረዋል።
ላቭሮቭ ለሩሲያ የዜና ወኪል ተናገሩ ብሎ ሮይተርስ እንደዘገበው ሞስኮ ደብዳቤውን ትመለከተዋለች ብለዋል።
ሩሲያ በተመድ እና በቱርክ አደራዳሪነት ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር የተደረሰው 'የጥቁር ባህር የእህል ስምምነት' እንዲቀጥል እንደማትፈልግ ፍንጭ ሰጥታለች። ለዚህም ሞስኮ በስምምነቱ መሰረት ወደ ውጭ የምትልካቸውን ምርቶች መላክ አለመቻሏ በምክንያት ተጠቅሷል።
ሀቅ ለፑቲን የተላከው ደብዳቤ "በቅርብ ጊዜ ተዋንያኑ ያሳዩትን አቋም እና ዓለም አቀፍ የምግብ ዋስትና እጦት የሚከሰቱትን አደጋዎች ከግምት ውስጥ ያስገባል" ብለዋል።
ተመሳሳይ ደብዳቤዎችም ወደ ዩክሬን እና ቱርክ መላካቸውን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።