ደቡብ አፍሪካ፣ ሩሲያ እና ቻይና የጋራ የባህር ኃይል ልምምዳቸውን ጀመሩ
ዛሬ የጀመረው የጋራ የባህር ኃይል ልምምዱ ለሚቀጥሉት 10 ቀናት የሚቆይ ይሆናል
መቀመጫቸውን ደቡብ አፍሪካ ያደረጉ ስድስት የአውሮፓ ህብረት ዲፕሎማቶች ልምምዱን አውግዘውታል
ደቡብ አፍሪካ ጦሯ ከሩሲያ እና ቻይና የጋር ወታደራዊ ልምምዶች እንደሚያደርግ በቅረቡ ይፋ አድርጋ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በተያዘው እቅድ መሰረት በወደብ ከተማዋ ደርባን ለ10 ቀናት የሚቆየው የጋራ የባህር ኃይል ልምምድ በዛሬው እለት ጀምሯል፡፡
የሩሲያው ከፍተኛ ዲፕሎማት ስለ “ደቡብ አፍሪካ-ሩሲያ የጋራ ወታደራዊ ልምምዶች” ምን አሉ ?
ይሁን እንጅ ልምምዱ ከጅምሩም ቢሆን በምዕራባውያን ዘንዳ ተቃውሞና ትችቶች እያስተናገደ መሆኑ የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል።
መቀመጫቸውን ደቡብ አፍሪካ ያደረጉ ስድስት የአውሮፓ ህብረት ዲፕሎማቶች ልምምዱን አውግዘውታል፡፡
እየሆነ ባለው ነገር ደስተኛ ያለሆኑት አንድ ዲፕሎማት "ትክክል አይደለም፤ እኛ (ምዕራባውያን) እንደማንቀበል ነገረናቸዋል" ማለታቸውንም ነው የተገለጸው፡፡
ደቡብ አፍሪካ በርካታ ትችቶችን ሲያስተናግድ የቆየውን ወታደራዊ ልምምድ በየትኛውም ዓለም የሚደረግ የተለመደ ነገር መሆኑ ስትገልጽ የቆየች ቢሆንም፤ ሀገሪቱ ከምዕራባውያን ጋር የነበራትን መልካም የሚባል ግንኙነት እንዳያሻክረው ተሰግቷል፡፡
ተንታኞች ልምምዱ ሞስኮ በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄድ ከጀመረችበት የመጀመሪያ አመት ጋር የመገናኘቱ አደገኛ ስልት መሆኑ ይናገራሉ፡፡
የደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተቋም ባልደረባ ስቲቨን ግሩዝድ “ልምምዶቹ የመብረቅ ዘንግ ይሆናሉ” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሪቶሪያ ከሞስኮ ጋር ወታደራዊ ልምምዶችን ከማድረግ የሚያስቆማት አንዳች ምክንያት እንደሌለ የደቡብ አፍሪካዋ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናለዲ ፓንዶር በቅርቡ መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ከሳምንት በፊት ከሩሲያው አቻቸው ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር ሆነው ለጋዜጣኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “አንዳንድ ሀገራት ከፈለጉት ሀገር ጋር ልምምድ እያረጉ ባሉበት ሁኔታ ሌሎችን መከልከል ተገቢ አይደለም” ሲሉ የምዕራባውያንን ትችት ውድቅ አድርገዋል፡፡
የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ የጋራ ልምምዱ “ፈረንሳይ፣ አሜሪካ እና የኔቶ አባ ሀገራት ከሚያካሂዱት ልምምድ የተለየ አይደለም” ብሎ ነበር፡፡
ዓለም ትኩረቱን ሁሉ ወደ ዩክሬን ቀውስ ባደረገበት በአሁኑ ወቅት የዓለም ኃያላን ሀገራት በአፍሪካ ለማስፈጸም የሚፈልጉትን ጥቅማቸው ለማስከበር ወደ አፍሪካ ማማተራቸው ቀጥለውበታል፡፡
የተባበሩት ምንግስታት በዩክሬን ጦርነት ጉዳይ ሩሲያን ለማውገዝ ከወራት በፊት ባሳለፈው የውሳኔ ሃሳብ ላይ አፍሪካውያን የጠራ አቋም ለመያዝ ሲቸገሩ የተስተዋሉበት አጋጣሚ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ደቡብ አፍሪካም ብትሆን ሩሲያን ባወገዘው ውሳኔ ላይ ድምጽ ከመስጠት ተቆጥባ እንደነበር ይታወሳል።