የሩሲያው ከፍተኛ ዲፕሎማት ስለ “ደቡብ አፍሪካ-ሩሲያ የጋራ ወታደራዊ ልምምዶች” ምን አሉ ?
ሰርጌ ላቭሮቭ ደቡብ ኣፍሪካ በዩክሬን ጉዳይ ላሳየችው “ሚዛናዊነት” ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል
ናለዲ ፓንዶር ደቡብ አፍሪካ የጋር ወታደራዊ ልምምዶችን ከማድረግ የሚያስቆማት አንዳች አካል የለም ብለዋል
ደቡብ አፍሪካ በቅርቡ ጦሯ ከሩሲያ እና ቻይና የጋር ወታደራዊ ልምምዶች እንደሚያደርግ ይፋ ማድረጓ አይዘነጋም፡፡
ይሁን እንጅ በመሚቀጥለው ወር ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ወታደራዊ ልምምድ ከአሁኑ በርካታ ትችቶች በማስተናገድ ላይ ነው፡፡
በጉዳዩ ላይ የተጠየቁት የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ሞስኮ በሚቀጥለው ወር ስለሚደረግ የጋራ ወታደራዊ የባህር ኃይል ልምምድ ሩሲያ ምንም ዓይነት “አሉባልታ” መስማት አትፈልግም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ሩሲያ ወታደራዊ ልምምዶችን በተመለከተ አስፈላጊውን መረጃ ሁሉ መስጠቷንም ጭምር ተናግረዋል፤ ሚኒስትሩ በፕሬቶሪያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፡፡
በተመሳሳይ የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናለዲ ፓንዶር ፕሪቶሪያ ከሞስኮ ጋር ወታደራዊ ልምምዶችን ከማድረግ የሚያስቆማት አንዳች ምክንያት የለም ብለዋል፡፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ከሩሲያው አቻቻው ጋር ሆነው ለጋዜጣኞች በሰጡት ማብራሪያ፤ “አንዳንድ ሀገራት ከፈለጉት ሀገር ጋር ልምምድ እያረጉ ባሉበት ሁኔታ ሌሎችን መከልከል ተገቢ አይደለም” ሲሉ በሀገራቸው ላይ የሚሰነዘረውን ትችት ውድቅ አድርገዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የደቡብ አፍሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ፤ ከሩሲያ ጋር ለማካሄድ የታቀደው የጋራ ልምምድ ፈረንሳይ፣ አሜሪካ እና የኔቶ አባ ሀገራት ከሚያካሂዱት ልምምድ የተለየ እንዳልሆነ አስታውቋል፡፡
እንደፈረንጆቹ ከየካቲት 27 ጀምሮ ለ10 ቀናት በወደብ ከተማዋ ደርባን የሚካሄደው የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ዋና ዓላማ ብቃትን ማእከል ያደረገ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ መሆኑም ገልጿል፡፡
ሩሲያ በየካቲት 24 ቀን በዩክሬን ያካሄደችውን ወታደራዊ ዘመቻን ተከትሎ ድርጊቱን ያወገዘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሩሲያ ጦር ከዩክሬን እንዲወጣ ላሰለፈው ውሳኔ የድጋፍ ድምጽ ካልሰጡት ሀገራት ደቡብ አፍሪካ አንዷ እንደነበረች አይዘነጋም፡፡
በዚህም የሩሲያው ከፍተኛ ዲፕሎማት ሰርጌ ላቭሮቭ ደቡብ ኣፍሪካ በዩክሬን ጉዳይ ላሳየችው “ሚዛናዊነት” ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡
የከፍተኛ ዲፕሎማቱ ላቭሮቭ በሰባት ወራት ወስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ አፍሪካ የመምጣት ሚስጥርም፤ ሩሲያ በምዕራቡ ዓለም ላይ ተጽእኖ ለመፍጠር እያደረገችው ላለው ጥረት የአፍሪካን አጋርነት ለማግኘት እንደሆነ በመገለጽ ላይ ነው፡፡
ላቭሮቭ ከወራት በፊት በነበረው የአፍሪካ ጉብኝታቸው ግብጽ፣ ኡጋንዳ፣ኮንጎ እን ኢትዮጵያን ጎብኝተው መመለሳቸው የሚታወስ ነው፡፡
ለይፋዊ የስራ ጉብኝት በደቡብ አፍሪካ የሚገኙት ላቭሮቭ በሀገሪቱ በሚኖራቸው ቆይታ ከሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነት፣ የጋራ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
እንደ ሩሲያ ቱደይ ዘገባ ከሆነ ከፍተኛ ዲፕሎማቱ ከሀምሌ 26 እስከ 29 በሩሲያ ሴንት ፒተርስበርግ በሚካሄደውና መሪዎች በሚሳተፉበት ሁለተኛው የሩሲያ- አፍሪካ ኢኮኖሚ ፎረም ዝግጅት ዙሪያም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ናለዲ ፓንዶር ጋር ይወያያሉ፡
በተጨማሪም ሁለቱም በአባልነት ባቀፈው የኢኮኖሚ ብሎክ (ብሪክስ) ሀገራት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ የሚመክሩ ይሆናል፡፡
የደቡብ አፍሪካ እና ሩሲያ ግንኙነት የቆየና ታሪካዊ እንደሆኑ ይነገራል፡፡ በተለይም ደቡብ አፍሪካውያን በጸረ አፓርታይድ ትግላቸው ከሩሰያ የስለላና ወታደራዊ ስልጠና ያገኙ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡