ሲሪል ራማፎሳ ለሁለተኛ ጊዜ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ተሸሙ
በ2024ቱ ምርጫ መንግስት ለመመስረት አብላጫውን ድምጽ ማግኝት ያልቻለው የፕሬዝዳንቱ ፓርቲ ከሌላ ፓርቲ ጋር ጥምር መንግስት ለመመስረት ተገዷል
ከራማፎሳ ጋር ፕሬዝዳንት ለመሆን የተፎካከረው አወዛጋቢው ጁሊየስ ማሌማ በፓርላማው 44 የድጋፍ ድምጽ አግኝቷል
ለቀናት መንግስት ለመመስረት በውዝግብ ውስጥ የቆየው የደቡብ አፍሪካ ፖለቲካ በመጨረሻም ሲሪል ራማፎሳን ለሁለተኛ ግዜ የስልጣን ዘመን ፕሬዝዳንት አድርጎ ተጠናቋል።
የማንዴላ አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ ከአፓርታይድ ማብቃት ከሶስተ አስርተ አመታት በኋላ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ በ2024ቱ ምርጫ መንግስት ለመመስረት የማያበቃውን ዝቅተኛ ድምጽ አግኝቷል።
ይህን ተከትሎ አጣማሪ መንግስት ፍለጋ በምርጫው ከተሳተፉ የተለያዩ ፓርቲዎች ጋር ንግግር ሲያደርግ የሰነበተው ኤኤንሲ በነጭ ደቡብ አፍሪካዊያን ከሚመራው ዴሞክራቲክ አሊያንስ ፓርቲ ጋር ለመጣመር ተስማምቷል።
ፓርላመንታዊ ስርአትን በምትከተለው ደቡብ አፍሪካ ፓርቲዎች ለምክር ቤቱ ወንበር ከተወዳደሩ በኋላ የምክር ቤት አባላቱ ፕሬዝዳንቱን ይሰይማሉ።
ሲሪል ራማፎሳ 400 መቀመጫዎች ባሉት ፓርላማ ከኢኤፍኤፍ ፓርቲ መሪው ጁሊየስ ማሌማ ጋር ለእጩነት የቀረቡ ሲሆን 283 የድጋፍ ደምጽ በማግኝት ለሁለተኛ ግዜ ሀገራቸውን የመምራት እድል አግኝተዋል።
ፕሬዝዳንቱ በፓርላማው ምርጫ ከፓርቲያቸው ኤኤንሲ በተጨማሪ በ2024ቱ ምርጫ ሁለተኛውን ከፍተኛ ድምጽ ካገኝው ዴሞክራቲክ አሊያንስ ሰፊ ድጋፍን አግኝተዋል። እራሱን በፓን አፍሪካኒስትነት የሚገልጸው ጁልየስ ማሌማ ዝቅተኛ የተባለውን 44 ድጋፍ አግኝቷል።
ጥምር መንግስት የመሰረቱት አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ እና ዴሞክራቲክ አሊያንስ ፓርቲ በርዕዮተ አለም እና በፖለቲካዊ አተያይ ፍጽም የተለያዩ ቢሆንም ደቡብ አፍሪካን በጋራ ለማስተደደር ተስማምተዋል።
ተንታኞች የነጻነት ታጋይ በነበረው ኤኤንሲ እና በለዘብተኛው ዲኤ መካከል ያለው ልዩነት ሰፊ መሆን ለራማፎሳ መንግስት መጽናት አደጋ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
ለአብነት ራማፎሳ በእስራኤል ጉዳይ ጠንካራ አቋም ይዘው በአለም ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ድረስ እንድትቀርብ እየጣሩ ቢሆንም አጣማሪው ፓርቲ ግን በዚህ ጉዳይ የተለየ አቋም ያለው ነው።
ራማፎሳ ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ ባደረጉት ንግግር “ይህ ለደቡብ አፍሪካ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ነው የተለያየ አቋም ቢኖረንም በደቡብ አፍሪካዊያን ደህንነት እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ዙርያ ተቀራርበን እንሰራለን” ብለዋል።