ደቡብ አፍሪካ ለሩሲያ መሳሪያ ልካለች ተብላ የቀረበባትን ውንጀላ ልመረምር ነው አለች
ሦስት አባላት ያሉት መርማሪ ቡድኑ በቀድሞ የዳኞች ምክትል ፕሬዝዳንት ይመራል
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ክሱ በደቡብ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ላይ ተጽዕኖ በማሳደሩ መመርመር አስፈልጓል ብለዋል
ደቡብ አፍሪካ ለሩሲያ መሳሪያ ልካለች ተብላ የቀረበባትን ውንጀላ ልመረምር ነው አለች።
አሜሪካ ባለፈው ታህሳስ ወር አንድ የሩሲያ መርከብ በኬፕታውን አቅራቢያ ከሚገኝ የባህር ኃይል የጦር መሳሪያ ሰብስቧል ስትል ወንጅላለች።
ውንጀላውን ተከትሎ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጉዳዩን የሚያጣራ ቡድን ሾመዋል።
በደቡብ አፍሪካ የአሜሪካ አምባሳደር ሩበን ብሪጌቲ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ታህሳስ ወር ላይ በምዕራብ ኬፕታውን ሲሞንስታውን የባህር ኃይል ጣቢያ ላይ የሩሲያ መርከብ ከደቡብ አፍሪካ የጦር መሳሪያ እንደወሰደ እርግጠኛ ነኝ ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
ደቡብ አፍሪካ ክሱን ውድቅ አድርጋለች።
ክሱ በአሜሪካ፣ በደቡብ አፍሪካ እና በሩሲያ መካከል ዲፕሎማሲያዊ አለመግባባቶችን የፈጠረ ሲሆን፤ ደቡብ አፍሪካ በዩክሬን ግጭት ላይ ያላትን አቋም አጠራጣሪ አድርጎታልም።
ደቡብ አፍሪካ ገለልተኛ ነኝ ስትል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጦርነቱ ላይ በተደረገ ውሳኔ ላይ ድምጽ ከመስጠት ተቆጥባለች።
"ፕሬዝዳንቱ የቀረበውን ክስ ለማቋቋም የወሰኑት የክሱ አሳሳቢነት፣ የህዝብ ጥቅም መጠን እና ይህ ጉዳይ በደቡብ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ላይ ስላሳደረው ተጽዕኖ ነው" ሲል የፕሬዝዳንት ጽ/ቤት በመግለጫው ጠቅሷል።
ሦስት አባላት ያሉት መርማሪ ቡድኑ በጋውቴንግ ግዛት የቀድሞ የዳኞች ምክትል ፕሬዝዳንት ፊንያስ ሞጃፔሎ ይመራል ተብሏል።
ምርመራውን ለማካሄድ ስድስት ሳምንታት እንደሚወስድ ሮይተርስ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንቱ ምርመራው በተጠናቀቀ በሁለት ሳምንታት ውስጥ የመጨረሻ ሪፖርት ይደርሳቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።