የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ አዲስ ፓርቲ መሰረቱ
ዙማ በ2024 በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ለመሰረቱት ኤኤንሲ ፓርቲ ድምጽ አልሰጥም ብለዋል
ደቡብ አፍሪካን ለ19 አመታት የመሩት ጃኮብ ዙማ በሙስና ወንጀል መከሰሳቸው ይታወሳል
የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ አዲስ ፓርቲ ማቋቋማቸውን ገለጹ።
ለ19 አመታት ደቡብ አፍሪካን በፕሬዝዳንትነት የመሩት ዙማ፥ በቀጣዩ ጠቅላላ ምርጫ ለመሰረቱት አፍሪካ ናሽናል ኮንግረንስ (ኤኤንሲ) እንደማይቀሰቅሱና ድምጽ እንደማይሰጡም ነው የተናገሩት።
“ኡምክሆንቶ ዊ ሲንዜ” ወይም በምህጻሩ “ኤምኬ” የሚል ስያሜ ያለው አዲስ ፓርቲያቸው የቀድሞውን የኤኤንሲ ወታደራዊ ክንፍ ስያሜ ወስዷል።
ዙማ አባል የነበሩበትና የአፓርታይድ አገዛዝን የተዋጋው ወታደራዊ ሃይል “ኤምኬ” በ1994 ኔልሰን ማንዴላ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው አንድ አመት ቀደም ብሎ መፍረሱ ይታወሳል።
ጃኮፕ ዙማ በሶዌቶ በሰጡት መግለጫ፥ የቀድሞው”ኤምኬ” በነፍጥ የአሁኑ “ኤምኬ” ደግሞ በምርጫ ይፋለማል ሲሉ ተናግረዋል።
“ራሳችን አሳልፈን የሰጠንለት ኤኤንሲ አሁን ተጠልፏል” የሚሉት ዙማ፥ በ2018 የተኳቸው ሲሪል ራማፎሳን ፓርቲውን ወደ ቁልቁለት እየገፉት ነው በማለት ወቅሰዋል።
“የራማፎሳ ኤኤንሲ በጥቁር ባለሙያዎች እና ምሁራን ላይ ጦርነት አውጇል፤ የታገልናቸው የነጭ የበላይነት አቀንቃኞች ወዳጅ ሆኗል” በሚልም ፓርቲውን ለመታደግ ትግል ጀምሬያለው ነው ያሉት።
በቀጣዩ ምርጫ ለኤኤንሲ ድምጽ መስጠትም የአፓርታይድ አገዛዝን እንደመደገፍና ህዝብን እንደመካድ ይቆጠራል ሲሉ ተደምጠዋል።
ዙማ አዲስ ፓርቲ ቢያቋቁሙም የኤኤንሲ አባል ሆነው እንደሚቀጥሉ መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ደቡብ አፍሪካ ባደረገችው የጸረአፓርታይድ አገዛዝ ትግል ውስጥ የተሳተፉትና ለአመታት በእስር ያሳለፉት አወዛጋቢው ሰው ጃኮብ ዙማ፥ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በ2018 ከስልጣናቸው መልቀቃቸው ይታወሳል።
በ2021ም በተከሰሱበት ወንጀል ፍርድ ቤት አልቀርብም በማለታቸው ለእስር መዳረጋቸው አይዘነጋም።
የዙማ እስር ከፍተኛ ተቃውሞና አመጽ አስነስቶ ከ350 በላይ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉና ከህክምና ጋር በተያያዘ ከሁለት ወራት ቆይታ በኋላ ከእስር መለቀቃቸው የሚታወስ ነው።
በዙማ የፕሬዝዳንትነት ዘመን ምክትላቸው የነበሩት ሲሪል ራማፎሳ ሙስናን ለመከላከል የያዙት አቋም በቀድሞው ፕሬዝዳንት የተወደደ አይመስልም።
ከስልጣን ቢነሱም በርካታ ተከታይ እንዳላቸው የሚነገርላቸው ጃኮብ ዙማ “ኤኤንሲን ከአፓርታይድ አቀንቃኞች ለመታደግ” በሚል አዲስ ፓርቲ አቋቁመው ራማፎሳ ላይ ተነስተውባቸዋል።
ከግንቦት እስከ ነሃሴ 2024 ባለው ጊዜ ውስጥ በሚደረገው ምርጫ በሙስና እና ብልሹ አሰራር ወቀሳው የበዛበት ኤኤንሲ ከሌሎች ፓርቲዎች ብርቱ ፉክክር ይጠብቀዋል ተብሏል።