የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጣር የወጣውን መመሪያ መጣስ እስከ 2 ዓመት በሚደርስ እስራት ያስቀጣል
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ ነው መመሪያ ቁጥር 30/2013 የወጣው
መመሪያው የእጅ መጨባበጥ እና ማስክ አለማድረግን ጨምሮ በርካታ ክልከላዎችን አካቷል
የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጣር የወጣውን መመሪያ መጣስ እስከ 2 ዓመት በሚደርስ እስራት ያስቀጣል
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ በአሁኑ ወቅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጣር የወጣ መመሪያ ቁጥር 30/2013 በተለያዩ አካላት ላይ ማለትም በግለሰቦች፣ በመንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና በድርጅቶች ላይ ክልከላዎችን እና ግዴታዎችን ጥሏል፡፡
ክልከላዎቹን መተላለፍ እና ግዴታዎቹን አለመወጣት አግባብ ባለው የወንጀል ህግ እንደሚያስቀጣ በመመሪያው ተደንግጎ እንደሚገኝ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡
ከኮቪድ -19 ወረርሽ የመተላለፍ ባህርይ አንፃር በመመሪያው ከተቀመጡ ክልከላዎች ለአብነት ያክል ለሰላምታና ለሌላ ለማንኛውም አላማ በእጅ መጨባበጥ፣ ሆነ ብሎ የእርስ በእርስ አካላዊ ንክኪ ማድረግ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አለማድረግ፣ በክፍት ገበያዎች፣ በትራንስፖርት መሳፈሪያ ቦታዎች፣ ህዝባዊ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ቦታዎችና ሌሎች ህዝብ በሚበዛባቸው መሰል አካባቢዎች ከሁለት የአዋቂ እርምጃ በታች ርቀት መቆምም ሆነ መቀመጥ፣ አገልግሎት ሰጪ የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማት ሰራተኞች ከሁለት የአዋቂ እርምጃ በታች ተጠጋግተው እና የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ፣ ተገልጋዮች በሚቀመጡበት ጊዜም ይሁን በማንኛዉም አኳኋን አገልግሎት ሲያገኙ ከሁለት የአዋቂ እርምጃ በታች ተጠጋግተው እና የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ወይም በአንድ ጠረጴዛ ከሶስት ተገልጋዮች በላይ እንዲቀመጡ ማድረግ ከክልከላዎቹ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ግዴታዎችን በተመለከተ ደግሞ የመንግስታዊ እና የግል ተቋማት አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ ተቋሙ ለሚመጡ ተገልጋዮች ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችሉ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን የማቅረብ፣ ለሰራተኞቻቸው የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የሚረዱ የጥንቃቄ ቁሳቁሶችን የማቅረብ፣ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረጋቸውን እና ሌሎች አስፈላጊ ጥንቃቄዎችን መተግበራቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለምሳሌ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በህግ በሚወሰነው የመጫን አቅም ልክ ሰዎችን የመጫን፣ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ያላደረጉ ሰዎችን አገልግሎት አለመስጠት፣ መስኮቶችን በመክፈት በተሽከርካሪው ውስጥ በቂ የአየር ዝውርውር እንዲኖር የማድረግ እና በዘርፉ በመመሪያ የሚወጡ ሌሎች መወሰድ የሚገባቸውን የጥንቃቄ እርምጃዎች በመተግበር አገልግሎት የመስጠት ግዴታዎች ይገኙበታል፡፡
ከላይ ለአብነት የተጠቀሱትን እና ሌሎች በመመሪያው የተካተቱ ክልከላዎችን እና ግዴታዎችን የተላለፈ ማንኛውም ሰው አግባብነት ባለው የወንጀል ህግ አንቀጽ መሰረት የሚቀጣ መሆኑን መመሪያው አንቀፅ 30 ላይ አስቀምጧል፡፡ ለጉዳዩ አግባብነት ያለው የወንጀል ህግ በ1996 ዓ.ም የወጣው የኢ.ፌ.ድ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 522 ነው፡፡ ይህም ጤናን ለመጠበቅና ለመንከባብ በህግ የተደነገጉትን የጥንቃቄ እርምጃዎችን መጣስ የሚያስከትለውን የእስራት እና የገንዘብ መቀጮ ይመለከታል፡፡
በዚህም መሰረት በወንጀል ህጉ አንቀፅ 522 ንዑስ አንቀፅ 1 ስር እንደተደነገገው ማንም ሰው ማለትም የተፈጥሮ ሰው ወይም በህግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ተላላፊ በሽታን ለመከላከል፣ ለመግታት ወይም ለማቆም በህግ የተደነገጉ የጥንቃቄ እርምጃዎችን አስቦ የጣሰ እንደሆነ ከሁለት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም በመቀጮ ይቀጣል፡፡ እንዲሁም ወንጀሉ የተፈፀመው በቸልተኝነት እንደሆነ ቅጣቱ ከስድስት ወር የማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከሦስት ሺህ ብር የማይበልጥ መቀጮ መሆኑን አንቀፅ 522/2 ይደነግጋል፡፡
መረጃውን ያገኘነው ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የፈፌስቡክ አድራሻ ነው፡፡