የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የደቡብ አፍሪካ ጉብኝት በርታ ስምምነቶች የተደረሱበት ነው፡፡
በ3 የደቡብ አፍሪካ ሃገራት ጉብኝት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል፡፡ በጊኒ ሪፐብሊክ እና በኢኳቶሪያል ጊኒ ቆይታ የነበራቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደቡብ አፍሪካም ይፋዊ የ2 ቀናት ጉብኝትን ካደረጉ በኋላ ነበር ወደ ሃገራቸው የተመለሱት፡፡
በደቡብ አፍሪካ በነበራቸው ቆይታም በአንጋፋው የሃገሪቱ መሪ ፓርቲ አፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ (ኤ.ኤን.ሲ) 108ኛው ክብረ በዓል ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል፡፡
ትናንት እሁድም በፕሪቶሪያ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋር ተወያይተዋል። በጆሃንስበርግ ኢምፔሪያል ዋንደረርስ ስቴዲየም ተሰባስበው ለነበሩ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎችም ንግግር አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዩኒዬን ቤተመንግስት ከፕሬዝዳንት ራማፎሳ ጋር በዘርፈ ብዙ የሁለትዮሽ እና ስትራቴጂካዊ የትብብር ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡ ከምክክሩ በኋላም መሪዎቹ በመከሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫን ሰጥተዋል፡፡
የመሪዎቹ የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ
ዶ/ር ዐቢይ ሃገራቸውን በመጎብኘታቸው ያደነቁት ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ግልጽና ሰፊ ፍሬያማ ውይይቶችን አድርገናል ብለዋል፡፡ ብዙ የሚጋሩት ታሪክ ያላቸው ሃገራቱ በፖለቲካዊና ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮች ላይ ይበልጥ ተቀራርበው ለመስራት መስማማታቸውንም ገልጸዋል፡፡
ከአሁን ቀደም የነበሩ ስምምነቶችንና የትብብር ማዕቀፎችን ከማደስ ባለፈ አዳዲስ ስምምነቶችንከመፈረም ባለፈ ግንኙነታቸውን ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማሳደግ መስማማታቸውንም ነው የተናገሩት፡፡ ከነዚህ ስምምነቶች መካከልም አንዱ የቪዛና ተያያዥ የፓስፖርት አገልግሎቶችን የሚመለከት ነው፡፡
ስምምነቱ ዲፕሎማሲያዊ እና ኦፊሴላዊ ፓስፖርት ለያዙ የሚሰጥ አገልግሎትን ይበልጥ ለማቅለልና ለማቀላጥፍ እንደሚያስችልም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡ ከቱሪዝም እና ከጤናው ዘርፍ በተጨማሪ በጸጥታና ደህንነት ጉዳዮች ተቀራርቦ ለመስራት የሚያስችላቸውንም ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ቆንጆ ያሏትን ደቡብ አፍሪካን እንዲጎበኙ የሃገሪቱ መንግስት ላቀረበላቸው ግብዣ ያመሰገኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው ከአመታት በፊት በተማሪነት የሚያውቋት ደቡብ አፍሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ለነጻነትና እኩልነት ሲደረግ ከነበረው ትግል ጀምሮ የጠበቀ ቁርኝት እንዳላት ተናግረዋል፡፡ ከፕሬዝዳንት ራማፎሳ ጋር መምከራቸው ይህንኑ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠንከር እንደሚያግዝም ነው የተናገሩት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ እየወሰደቻቸው ያሉ ሃገር በቀል የምጣኔሃብት ማሻሻያዎች ትብብርን የሚፈልጉና የሚጋብዙም ናቸው ያሉም ሲሆን በምጣኔ ሃብትና በፖለቲካዊ ዘርፎች ከሚደረጉ ግንኙነቶች ጎን ለጎን የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን ማጠናከር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡ደቡብ አፍሪካውያን ሊሳተፉባቸው የሚችሉ የግል ኢንቨስትመንት መስኮች መመቻቸታቸውን ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዳሴው ግድብና ከኖቤል የሰላም ሽልማት ጋር በተያያዘ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥዋል፡፡
ከኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ጋር የነበራቸው ቆይታ
ዶ/ር ዐቢይ በጆሃንስበርግ ኢምፔሪያል ዋንደረርስ ስቴዲየም ተሰባስበው በጉጉት ሲጠብቋቸው ከነበሩ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎችም ጋር
ተገናኝተዋል፡፡
ከፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋር የነበራቸውን የውይይት ጊዜ ጨምሮ ወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮችን የተመለከተ ንግግር አድርገዋል።
የውጭ ጠላትን ለማሸነፍ ከመነሳታችን በፊት የውስጥ ጠላት የሆኑትን ጥላቻና ቂም ማሸነፍ ይኖርብናል ያሉት ዶ/ር ዐቢይ ዋና ጠላት ያሉትን ስንፍናን ለማሸነፍ ተግቶ መስራት ይገባልም ብለዋል፡፡ ለዚህም ዜጎች ሃብታቸውን በሃገር ውስጥ ፈሰስ በማድረግ ህዝባቸውን እንዲያገለግሉም ገልጸዋል፡፡
ዳያስፖራው በአንድነት በመቆም ክብሩንና ታሪኩን እንዲያስጠብቅም ጠይቀዋል፡፡የዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት ጊዜው አሁን ነው ያሉም ሲሆን ሁሉ በመተባበር ሊለማመደው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ለመጪው ሃገራዊ ምርጫ ወድማማችነት እንደሚያስፈልግም ነው የተናገሩት፡፡
ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች በደቡብ አፍሪካ ጥሩ ስም እንዳላቸው የገለጹት ዶ/ር ዐቢይ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ጉዳዮች ለመከታተል የሚያችል ጥምር ኮሚቴ ለማቋቋም ስለመስማማታቸው ገልጸው የኮሙኒቲው ተወካዮች ከፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋር የሚመክሩበት ሁኔታ እንደሚመቻችም ተናግረዋል፡፡
የጉብኝቱ አንድምታ
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደቡብ አፍሪካ ጉብኝት የተሳካ እንደነበር በመንግስት ተገልጿል፡፡ እሳቸውም በጉብኝታቸው የተደረጉ ስምምነቶችን ሁሉ በቅርበት እንደሚከታተሉ በስማቸው ባለው የፌስቡክ ገጽ አስታውቀዋል፡፡ በእርግጥ በጎበኟቸው ሃገራት ሁሉ የተደረጉት ስምምነቶች ይበልጥ ተደጋግፎ ለመስራት የሚያስችሉ ናቸው፡፡
ጉብኝቱ ከዚህም በላይ ትርጉም ያለው ነው፡፡ በተለይ የደቡብ አፍሪካው ልዩ ትርጉም የሚሰጠው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በርከት ያሉ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች እዛው የሚኖሩ መሆናቸው እና አሁን አሁን በደቡብ አፍሪካውያኑ ዘንድ ተዘውትረው የሚስተዋሉ የመጤ ጠል እሳቤዎች (ዜኖፎቢያ) መኖራቸው የጉብኝቱን አስፈላጊነት ያጎላዋል፡፡ ዶ/ር ዐቢይም ይኸው ጉዳይ እልባት ሊያገኝ የማይችል ካልሆነ በስተቀር በሚል ምክንያት ከአሁን ቀደም የመጡላቸውን የጉብኝት ግብዣዎች ሳይቀበሉ ስለመቅረታቸው ሲነገር ነበር፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ተቀዳሚ አጀንዳ ይሄው እንደሆነም አምባሳደር ብርቱካን አያኖን ዋቢ አድርጎ አብመድ ዘግቦ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዜጋ ተኮር መሆን እንዳለበት አበክረው ከመናገርም በላይ በፖሊሲ ማሻሻያው ትኩረት እንዲያገኝ እየሰሩ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህንኑ ሃሳብ ያሳኩት ይመስላል፡፡ የዳያስፖራውን ጉዳይ የሚከታተል ጥምር ኮሚቴ ለማቋቋም ስለመስማማታቸውም ገልጸዋል፡፡ ይህ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ነው፡፡
የአፍሪካ ህብረት በቅርቡ በሚያካሂደው ዓመታዊ የመሪዎች ጉባዔ የህብረቱን የሊቀመንበርነት ቦታ ከምትቆናጠጠው ሃገር ጋር ይበልጥ መወዳጀቱም ወቅቱን የሚዋጅ ነው፡፡ በአጠቃላይና የህብረቱ የህልውነት ጉዞ የጎላ አበርክቶ ያላት ሃገር ወደፊት በቀጣናዊና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ መጫወት ለምትፈልገው ሚናም ምቹ መደላድልን ይፈጥራል፡፡ራሷ በሊቀመንበርነት በምትመራው ህብረት ሳትተማመን ቀርታ ወደ ምዕራባውያን ከምታንጋጥጠው ግብጽ ሊደርስባት የሚችለውን ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለማርገብም ያስችላታል፡፡
ዶ/ር ዐቢይ በህዳሴው ግድብ ጉዳይ እንዲያሸማግሏቸው ፕሬዝዳንት ራማፎሳን ስለመጠየቃቸውም ኤስ.ኤ.ቢ.ሲ የተሰኘው የሃገሪቱ ብዙሃን መገናኛ አስነብቧል፡፡