የኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ከነገ ጀምሮ በደቡብ ኮሪያ ጉብኝት ያደርጋሉ
ኤምሬትስ ከደቡብ ኮሪያ ጋር ልዩ ስትራቴጂካዊ ትብብር በመመስረት ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ቀዳሚዋ ናት
አባዳቢ በቀጣዮቹ ጥቂት አመታት በደቡብ ኮሪያ 30 ቢሊየን ዶላር ኢንቨስት ለማድረግ ማቀዷን ባለፈው አመት ይፋ ማድረጓ ይታወሳል
የአረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ በደቡብ ኮሪያ የመጀመሪያ ይፋዊ ጉብኝታቸውን በነገው እለት ይጀምራሉ።
ፕሬዝዳንቱ ይፋዊ ጉብኝቱን የሚያደርጉት በደቡብ ኮሪያ አቻቸው ዮን ሱክ የል በተደረገላቸው ግብዣ ነው።
በሴኡል የሁለት ቆይታ የሚያደርጉት ፕሬዝዳንት ሼክ ሞሀመድ ቢን ዛይድ በንግድ፣ ኢንቭስትመንት፣ ኢነርጂ እና ቴክኖሎጂ ዘርፎች የሀገራቱን ትብብር የሚያሳድጉ ምክክሮችን እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ከደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል ጋር በሚኖራቸው ቆይታ ከሁለትዮሽ ባሻገር በቀጠናዊ እና አለማቀፋዊ ጉዳዮች ላይም ምክክር ያደርጋሉ።
የኤምሬትስና ደቡብ ኮሪያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት
ደቡብ ኮሪያ በፈረንጆቹ ሰኔ 1980 በአቡዳቢ ኤምባሲዋን ስትከፍት ነው የሀገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመረው።
ኤምሬትስ ደግሞ ከሰባት አመት በኋላ (1987) ኤምባሲዋን በሴኡል የከፈተች ሲሆን፥ በ2010 የወታደራዊ አታሼ ቢሮዋን ከፍታለች።
ሲኡል በታህሳስ ወር 2007 በዱባይ ቆንስላዋን እንዲሁም በ2016 በአቡዳቢ የባህል ማዕከሏን መክፈቷም የሀገራቱን ትስስር ይበልጥ አሳድጎታል።
ኤምሬትስ ከደቡብ ኮሪያ ጋር ልዩ ስትራቴጂካዊ ትብብር በመመስረት ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ቀዳሚዋ ናት።
ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች፣ በኒዩክሌር ልማት፣ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል፣ በሳይበር ደህንነት እና ምግብ ዋስትና በትብብር በመስራት ላይ ናቸው።
በደህንነት፣ በጤና ጥበቃ፣ ባህል እና በመንግስት አስተዳደር በጋራ የሚያከናውኗቸው ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን የኤምሬትስ መንግስት ይገልጻል።
የቀድሞው የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ሙን ጃይ ኢን በመጋቢት 25 2018 በኤምሬትስ ጉብኝት ሲያደርጉም ሀገራቱ ግንኙነታቸውን ወደ ልዩ ስትራቴጂካዊ ትብብር ማሳደጋቸው ይታወሳል።
የውቅቱ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ የልም ባለፈው አመት በኤምሬትስ ጉብኝት ማድረጋቸው አይዘነጋም። በዚሁ ወቅትም የኤምሬትሱ “ታዋዙን ካውንስል” ከደቡብ ኮሪያው “ኮሪያን ኤሮስፔስ ኢንዱስትሪስ ሊሚትድ” ጋር የጭነት አውሮፕላኖችን ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
የኤምሬትስ ባለስልጣናትም ባለፉት ሁለት አመታት ስትራቴጂካዊ ግንኙነቱን የሚያጠናክሩ ጉብኝቶችን በሴኡል አድርገዋል።
በቀጣዮቹ ጥቂት አመታት በደቡብ ኮሪያ 30 ቢሊየን ዶላር ኢንቨስት ለማድረግ ያቀደችው ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ የሁለት ቀናት የሴኡል ጉብኝትም የሀገራቱን ልዩ ስትራቴጂካዊ ትስስር እንደሚያጎለብት ይጠበቃል።