ደቡብ ኮሪያ በሀገር ውስጥ በሰራችው ሮኬት ሳተላይት ልታመጥቅ ነው
ሴኡል በዛሬው እለት የምታመጥቀው ሳተላይት የወታደራዊ አገልግሎት እንደማይሰጥ ገልጻለች
ሰሜን ኮሪያ በበኩሏ በቅርቡ ወታደራዊ ሳተላይት ለማምጠቅ ተዘጋጅታለች ተብሏል
ደቡብ ኮሪያ ከወታደራዊ ግልጋሎት ውጭ የሚውል ሳተላይቷን ዛሬ ምሽት ወደ ህዋ ታመጥቃለች።
- የአሜሪካ ሳተላይት ወደ ምድር እየተምዘገዘገች እንደሆነ ተገለጸ
- ሰሜን ኮሪያ አህጉር አቋራጭ ባላስቲክ ሚሳይል ማስወንጨፏን ተከትሎ አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ የጋራ የአየር ልምምድ አደረጉ
ሳተላይቷ በደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍል ከሚገኘው “ኑሪ የህዋ ማዕከል” ነው በሀገር ቤት በተሰራ ሮኬት ወደ ህዋ ትመነጠቃለች የተባለው።
የሀገሪቱ የሳይንስ ሚኒስቴር “ኔክስት ጀነሬሽን ስሞል ሳተላይት 2” የተሰኘችው ሳተላይት በምድር አናት ላይ ሆና የራዳር ምስሎችን የማረጋገጥ ተልዕኮ ተሰጥቷታል።
የሳተላይቷ ተልዕኮም ከወታደራዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ምስሎችን መላክ እንዳልሆነ ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ተንታኞች ግን ሴኡል ዛሬ የምታምጥቃት ሳተላይት በቀጣይ ወታደራዊ ሳተላይት ለማምጠቅ ለምታደርገው ዝግጅት ፈር ቀዳጅ እንደሚሆን መናገራቸውን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
ጎረቤቷ ሰሜን ኮሪያ በሰኔ አልያም በሀምሌ ወር የስለላ ሳተላይት እንደምታመጥቅ ተገልጿል።
የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡንም ባለፈው ሳምንት ለመምጠቅ ዝግጅቷን የጨረሰችውን ሳተላይት መጎብኘታቸው የሚታወስ ነው።
ፒዮንግያንግ ለመጀመሪያ ጊዜ የምታመጥቃት የስለላ ሳተላይት የኮሪያ ልሳነ ምድርን ወለል አድርጋ እንደምታሳይ ይጠበቃል።
ይህም ከጎረቤቷ ጋር የህዋ ላይ ፉክክር ውስጥ ከማስገባት አልፎ የቀጠናውን ውጥረት እንዳያባብሰው ተሰግቷል።
ደቡብ ኮሪያ “ኑሪ” በተሰኘችው ሮኬት በ2022 ሳተላይት ያመጠቀች ሲሆን፥ ይህም በራሷ ሮኬት ሳተላይት ያመጠቀች 10ኛዋ የአለማችን ሀገር አድርጓታል።
እስካሁን የራሷ ወታደራዊ ሳተላይት የሌላት ደቡብ ኮሪያ የሳተላይት ምስሎችን ከአሜሪካ እንደምታገኝ ይታወቃል።