የአሜሪካ ሳተላይት ወደ ምድር እየተምዘገዘገች እንደሆነ ተገለጸ
ሳተላይቷ ላለፉት 38 ዓመታት በጠፈር ላይ በመሬት እንቅስቃሴ ዙሪያ መረጃ ስትስበስብ ቆይታለች ተብሏል
ሳተላይቷ በኮሪያ ባህረ ሰላጤ ላይ ልትርፍ እንደምትችል ተገምቷል
የአሜሪካ ሳተላይት ወደ ምድር እየተጓዘች እንደሆነ ተገለጸ፡፡
የደቡብ ኮሪያ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንደገለጸው ከአገልግሎት ውጪ የሆነች የአሜሪካ ሳተላይት ወደ ምድር እየተምዘገዘገች ነው፡፡
ላለፉት 38 ዓመታት በጠፈር ላይ ሆና የመሬትን እንቅስቃሴ በሚመለከት መረጃዎችን ስትሰበስብ የቆየችው ይህች ሳተላይት አሁን ላይ ከአገልግሎት ውጪ እንደሆነች ተገልጿል፡፡
ሳተላይቷ በኮሪያ ባህረ ሰላጤ ላይ ልታርፍ ትችላለች መባሉን ተከትሎ የደቡብ ኮሪያ መንግስት ዜጎች ከሳተላይቷ ስብርባሪ ራሳቸውን እንዲጠብቁ አሳስቧል፡፡
450 ኪሎ ግራም እንደምትመዝን የተገለጸችው ይህች ሳተላይት ንብረትነቷ የአሜሪካው ናሳ የተሰኘው የጠፈር ምርምር ተቋም ስትሆን በእርጅና ምክንያት አገልግሎት ማቋረጧ ተገልጿል፡፡
ናሳ ከዚህ በፊት ወደ ምድር የሚመጡ የሳተላይት ስብርባሪዎች ከ9 ሺህ 400 ሰዎች ውስጥ በአንድ ሰው ላይ አደጋ የማድረስ እድል አላቸው ሲል ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡
የጠፈር ምርምር የብዙ ሀገራትን ትኩረት እየሳበ ያለ ዘርፍ ሲሆን ሀገራትም የጠፈር ላይ የበላይነትን ለመያዝ ፉክክራቸው እየጨመረ መምጣቱ ይገለጻል፡፡
በተለይም ቻይና አሜሪካ የጠፈር ላይ የበላይነትን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ፉክክር ውስጥ ያሉ ሲሆን በየጊዜው እና በተደጋጋሚ ሳተላይቶችን ወደ ጠፈር በማምጠቅ ላይ ናቸው፡፡
ሳተላይቶች የሰው ልጆችን ህይወት ቀላል በማድረግ የሚታወቁ ሲሆን በተለይም የኮሙንኬሽን ሳተላይቶች ዘመናዊ እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለመለዋወጥ ትልቅ ሚና አላቸው፡፡