ሰሜን ኮሪያ አህጉር አቋራጭ ባላስቲክ ሚሳይል ማስወንጨፏን ተከትሎ አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ የጋራ የአየር ልምምድ አደረጉ
ደቡብ ኮሪያ ልምምዱን የተቀናጀ የተልዕኮ አቅምን ያጠናከረ ብላዋለች
የቅዳሜው ሚሳይል ለሰሜን ኮሪያ ከአዲሱ የፈረንጆች ዓመት ወዲህ የመጀመሪያው ነው
ሰሜን ኮሪያ ህዋሶንግ-15 የተሰኘ አህጉር አቀፍ ባሊስቲክ ሚሳይልን ከተኮሰች ከአንድ ቀን በኋላ አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ ስልታዊ ቦምቦችን ያሳተፈ የጋራ የአየር ልምምድ አድርገዋል።
የሀገራቱ ተዋጊዎች አውሮፕላኖች የተሳተፉበት ልምምዱ የአጋሮቹን “አስደንጋጭ” የመከላከል አቅም እና ዝግጁነት አሳይቷል ተብሏል።
ልምምዱ የተቀናጀ የተልዕኮ አቅምን ያጠናከረ ተብሎለታል።
አሜሪካ የኮሪያን ሰርጥ ለመከላከል ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጧል ሲል የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ኃይል በመግለጫው ተናግሯል።
የጃፓኑ ፉጂ የዜና አውታር እንዳስታወቀው ጃፓንና አሜሪካ እሁድ ከሰአት በኋላ የጋራ የአየር ልምምድ ሊያደርጉ እንደሚችሉም ገልጿል።
የአሜሪካ-ደቡብ ኮሪያ ልምምድ ሰሜን ኮሪያ በጃፓን ምዕራባዊ የባህር ጠረፍ ላይ የረዥም እርቀት ሚሳይልን ከወረወረችና ለሀገራቱ ወታደራዊ ልምምዶች ጠንከር ያለ ምላሽ እንደምትሰጥ ማስጠንቀቋን ተከትሎ የመጣ ነው።
የሰሜን ኮሪያ ብሄራዊ ሚዲያ ኬሲኤንኤ አዲሱን ሚሳይል "በጠላት ኃይሎች የሚደርስን የኒውክሌር ጥቃት ለመቀልበስ ተጨባጭ ማስረጃ ነው" ብሏል።
የቅዳሜው የሚሳይል ለሰሜን ኮሪያ ከአዲሱ የፈረንጆች ዓመት ወዲህ የመጀመሪያ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል ።
ሚሳይሉ ለአንድ ሰአት ከስድስት ደቂቃ ከ55 ሰከንድ በላይ አምስት ሽህ 768 ኪ/ሜ መብረሩን የሀገሪቱ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ህዋሶንግ -15 ለመጀመሪያ ጊዜ ሙከራ የተደረገው በፈረንጆች 2017 ነው።