ደቡብ ኮሪያ በስራ ማቆም አድማ ላይ የሚገኙ ዶክተሮችን እንደምታስር አስጠነቀቀች
9 ሺህ የሚጠጉ በስራ ላይ ስልጠና የሚገኙ ዶክተሮች አድማ ከጀመሩ ዛሬ 11ኛ ቀናቸውን ይዘዋል
ሴኡል በ10 አመት ውስጥ 10 ሺህ ዶክተሮችን አስተምራ ወደ ስራ ለማስገባት አቅዳለች
ደቡብ ኮሪያ በስራ ማቆም አድማ ላይ የሚገኙ ዶክተሮችን እንደምታስር አስጠነቀቀች።
ተመርቀው በስራ ላይ ስልጠና የሚገኙት 8 ሺህ 900 ዶክተሮች ወደ ስራ እንዲመለሱ የተቀመጠላቸው የመጨረሻ ቀን ዛሬ ነው ተብሏል።
እስካሁን 300 ዶክተሮች ወደ ስራቸው ተመልሰዋል ያለው የሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴር፥ ቀሪዎቹ ዛሬ ካልተመለሱ የስራ ፈቃዳቸውን በጥቂቱ ለሶስት ወራት እንደሚሰርዝባቸው ገልጿል።
በስራ ማቆም አድማው ምክንያት በርካታ ሆስፒታሎች የቀዶ ህክምና አቅማቸው በግማሽ መቀነሱና ከፍተኛ ችግር እንደገጠማቸው ነው የተነገረው።
የደቡብ ኮሪያ መንግስት በቀጣዩ አመት ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ የህክምና ተማሪዎች ቁጥር ከ3 ሺህ ወደ 5 ሺህ ያድጋል የሚል እቅድ ማውጣቱ ነው ዶክተሮቹን ስራ አስቁሞ አደባባይ ያስወጣው።
ሴኡል እስከ 2035 ድረስ 10 ሺህ ዶክተሮችን ለማስመረቅና ወደ ስራ ለማስገባት የያዘችው እቅድ የህክምና ጥራትን ችግር ውስጥ የሚከት ነው፤ ውሳኔው አቅም የሌላቸው ሁሉ ዘርፉን እንዲቀላቀሉም ሊያደርግ ይችላል የሚሉ አስተያየቶችን ሰጥተዋል ተቃውሞ ያነሱት ዶክተሮች።
ተቺዎቻቸው ደግሞ በርካታ ዶክተሮች መመረቃቸው ተፈላጊነታቸውን ቀንሶ በገቢያቸውም ላይ ተጽዕኖውን በማሰባቸው ነው አደባባይ የወጡት ይላሉ።
በደቡብ ኮሪያ ያለው የዶክተር ለታካሚ ምጣኔ 2 ነጥብ 1 ለ1 ሺህ ነው፤ ይህም ካደጉት ሀገራት አማካይ (3 ነጥብ 7 ለ1 ሺህ) በጣም ዝቅ ያለ ነው።
የአለማችን ዝቅተኛው የውልደት ምጣኔ ክብረወሰንን የያዘችው ሴኡል ወደ እርጅና የሚሸጋገረው ህዝቧ እየጨመረ ከመሄዱ ጋር ተያይዞም የህክምና ባለሙያዎችን ቁጥር ማሳደግ ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል።
ከፈረንጆቹ የካቲት 20 2024 ጀምሮ የስራ ማቆም አድማ ላይ የሚገኙት 9 ሺህ የሚጠጉ ዶክተሮች ግን ጥያቄያችን ካልተመለሰ ወደ ስራ ገበታችን አንመለስም ማለታቸውን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።